22 ባለጸጋ ወንዶች በድምሩ ካጠቃላይ አፍሪካ ሴቶች በላይ ሀብት እንዳላቸው ኦክስፋም ይፋ አደረገ፡፡
በአለም የኢኮኖሚ ሲስተም ሴቶች ከፍተኛ መገለል እንደሚስተዋልባቸው የ20 ተራድኦ ድርጅቶች ኮንፈዴሬሽን የሆነው አክስፋም ይፋ ያደረገው ጥናት ያሳያል፡፡
ጥናቱ 22 ባለሀብት ወንዶች በድምሩ ካጠቃላይ የአፍሪካ 326 ሚሊዮን ሴቶች በላይ ሀብት እንደያዙ ያሳያል፡፡
ከ1% በታች የሆኑ የዓለማችን ባለሀብቶች ደግሞ ከመላው የዓለም 6.9 ቢሊዮን ህዝብ ከ2 እጥፍ በላይ ሀብት እንዳላቸው በጥናቱ ሪፖርት ተጠቁሟል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት የቢሊየነሮች ቁጥር እጥፍ ሆኗልም ይላል የኦክስፋም ጥናት፡፡
የዓለም መሪዎች ነገ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚጀመረው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ በማሰብ ነው ግብረሰናይ ድርጅቱ የጥናቱን ውጤት ይፋ ያደረገው፡፡ በተለይም ቤተሰብን የመንከባከብ ኃላፊነትን የሚወጡ የዓለማችን ሴቶችን ጫና ማቃለል የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲዘጋጁ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
እድሜያቸው 15 እና ከዛ በላይ የሆኑ ሴቶች ያለክፍያ የሚያከናውኑት የቤተሰብ እንክብካቤ አገልግሎት፣ በገንዘብ ቢተመን በዓመት ከ10.8 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚሆንም በኦክስፋም 63 ገጽ ሪፖርት ላይ ተብራርቷል፡፡
ጥናቱን መነሻ በማድረግ፣ በዓለማችን የሚስተዋለው የኢኮኖሚ ልዩነት በዋናነት ከጾታ እኩልነት ችግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ኦክስፋም አስታውቋል፡፡
መንግስታት ነጻ የህዝብ አገልጎሎቶችን በመስጠትና በባለጸጋዎች ላይ ከፍተኛ ግብር በመጣል የኢኮኖሚ ልዩነቶችን ለማጥበብ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ኦክስፋም ምክሩን ለግሷል፡፡
የባለሀብቶችን ጫናና ተጽእኖ ለመከላከልም መንግስታት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ባለሀብቶች ለማህበረሰቡ ይጠቅማሉ ወይስ አይጠቅሙም በሚል በተለያዩ ሀገራት ክርክሮች በሚደረጉበት ወቅት ነው ሪፖርቱ የወጣው፡፡
ለ4 ቀናት የሚቆየው 50ኛውየዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በዳቮስ ነገ ይጀምራል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም እና አፍሪካ የኢንቨስመንት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ጥር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ለንደን ያቀኑት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በጉባኤው ለመታደም ነገ ከለንደን ወደ ስፍራው ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን