እስራኤል ከሁለት ወራት ተኩስ አቁም በኋላ በጋዛ ድጋሚ ሙሉ ጦርነት ማወጇን አስታወቀች
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የትናንቱን መጠነ ሰፊ ጥቃት “ገና መጀመሩ ነው” ሲሉ ዝተዋል

በትላንቱ ጥቃት የሀማስ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ400 በላይ ንጹሀን ተገድለዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ሙሉ ጦርነት መጀመሩን ትላንት ምሽት በቴሌቪዠን ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት በጋዛ የተለያዩ አካባቢዎች ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ400 በላይ ንጹሀን መሞታቸውን እና አሁንም በፍርስራሾች ውስጥ አድራሻቸው የጠፉ ሰዎች መኖራቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ አመላክቷል፡፡
በቤት ላሂያ ፣ ራፋህ፣ ኑሲይራት እና አል-ማዋሲ ላይ የደረሰው የአየር ድብደባ የጋዛ ነዋሪዎች ከጥር ጀምሮ አግኝተውት የነበረውን አንፃራዊ ሰላም ያደፈረሰ እና ሆስፒታሎችም በድጋሚ በተጎጂዎች እንዲሞሉ ያደረገ ነው።
ኔታንያሁ ከዚህ ጥቃት በኋላ በሰጡት መግለጫ “ይህ ገና ጅማሬው ነው በውግያ ውስጥ ሆነን ድርድራችንን እንቀጥላልን” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እስራኤል በሀማስ ስር የሚገኙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ለሀማስ ያቀረበቻቸው የስምምነት ሀሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ወደ ውጊያ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
“ሁሉምን ታጋቾች ለማስመለስ ፣ ሀማስ ለእስራኤል ስጋት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና ለማጥፋት እንዲሁም ሁሉንም የጦርነት ግቦቿን ለማሳካት እስራኤል ትግሏን ትቀጥላለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከጅምሩ በርካታ ፈተናዎች በዝተውበት የነበረው ጊዜያዊ ተኩስ አቁም በሺዎች ለሚቆጠሩ ፍልስጤማውን እስረኞች እና ለታጋቾች መለቀቅ ምክንያት መሆን ችሎ ነበር፡፡
የመጀመሪያው የተኩስ አቁም ምዕራፍ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ካበቃ በኋላ ሁሉቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ወደፊት እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል አልተስማሙም።
ይህን ተከትሎ የትላንቱ ጥቃት በዘላቂነት ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ተስፋ ያጨለመ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል በሚደረገው ድርድር ከሚሳተፉ አካላት መካከል አንዱ የሆኑት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ታሚም ካሊፍ “የአየር ጥቃቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በግልጽ የጣሰ የወራት የድርድር ጥረትን ያከሰረ ነው” ብለውታል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ብሪያን ሂዩዝ በበኩላቸው “ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም ታጋቾችን ሊፈታ ይችል ነበር ይልቁንም እምቢተኝነትን እና ጦርነትን መርጧል” ብለዋል።
እስራኤል በመጀመሪያው ዙር ስምምነት መሰረት ወታደሮቿን ከጋዛ በምታስወታበት ሂደት እና በዛላቂ ጦርነት ማቆም ዙሪ ከሀማስ ጋር በአሁኑ ወቅት እንደምትደራደር ስትጠበቅ ሙሉ ጦርነት አውጇል፡፡
ይህም ከ15 ወራት በላይ የዘለቀውን የፍልስጤማውን ሰቆቃ ዳግም እንደሚያስጀምር በአከባቢው ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ይበልጥ አስከፊ እንደሚያደርገው እየተዘገበ ነው፡፡