አቃቢ ህግ በእነ ዮሀንስ ቧያለው መዝገብ ስር በተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክሮችን ማሰማት ጀመረ
በዚህ መዝገብ ስር 52 ተጠርጣሪዎች የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል

አቃቢ ህግ ተከሳሾቹ ባስተላለፉት ትዕዛዝ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች አቅርቧል
አቃቤ ህግ በእነ ዮሀንስ ቧያለው መዝገብ ስር በተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክሮችን ማሰማት ጀመረ።
የፍትህ ሚኒስቴር በእነ ዮሀንስ ቧያለው መዝገብ ባሉ 52 ተጠርጣሪዎች ላይ የፖለቲካ ርዕዮትን በሀይል ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፣ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ እንዲሁም የሽብር ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣውን ህግ ጥሰዋል በሚል ከአንድ ዓመት በፊት ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
በዚህ ክስ መዝገብ ስርም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ እንዲሁም የአማራ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የክልሉ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሀንስ ቧያለው እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሸገር (ዶ/ር) ጫኔ ከበደ፣ እስክንድር ነጋ፣ ዘመነ ካሴ፣ አበበ ፈንታው፣ አሰግድ መኮንን፣ መከታው ማሞ፣ ፈንታሁን ሙሃባ እና ሌሎችም ተካተዋል፡፡
ከ52ቱ ተከሳሾች መካከል 16ቱ ተከሳሾች አዲስ አበባ ልደታ በሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህገ መንግስት እና ሽብር ወንጀሎች ችሎት የቀረቡ ሲሆን የአቃቢ ህግ ምስክሮች በተከሳሾች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን እንደሰጡ የተከሳሾች ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ጠበቃ ሰለሞን እንዳሉት በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛና 2ተኛ ህገ-መንግስታዊ እና ፀረ -ሽብር ችሎት አቃቤ ህግ በእነ ዮሐንስ ቧያለው የክስ መዝገብ በሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረባቸውን ምስክሮች ፍርድ ቤቱ መስማት ጀምሯል፡፡
በመዝገቡ ከተዘረዘሩት 52 ተከሳሾች መካከል 16ቱ ብቻ ክሳቸውን በችሎት ቀርበው እየተከታተሉ ነው ያሉት ጠበቃው አቃቢ ህግ አሉኝ ካላቸው 21 ምስክሮች መካከል ስምንቱን በችሎቱ አቅርቦ ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ተደርጎ የምስክር ቃል ተሰምቷልም ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ሌሎች 15 ምስክሮችን እስከ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ መስማቱን እንደሚቀጥል ጠበቃ ሰለሞን አክለዋል።
እንደ ጠበቃ ሰለሞን ገለጻ የአቃቢ ህግ ምስክሮች በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር ዙሪያ ሀምሌ 29 ቀን 2015 ዓ. ም በፌደራል ፖሊስ አባላት እና ታጣቂዎች መካከል ተካሂዷል በተባለ ውጊያ የደረሱ ጉዳቶችን የሚያስረዱ ምስክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል።
አቃቢ ህግ ምስክሮቹን ተካሳሾች በቀጥታ ያደረሱትን ጉዳት እንዲያስረዱ ያቀረባቸው ቢሆንም እስካሁን የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት ምስክሮች እስካሁን ተከሳሾችን እንደማያውቋቸው እና በእነሱ ላይ ለመመስከር ችሎት እንዳልቀረቡ ነገር ግን በወቅቱ በክልሉ (ባህርዳር) ስለተፈጠረውን ነገር መመስከራቸውን ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
ምስክሮቹ በተጠቀሰው ዕለት በታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት አብረዋቸው የጸጥታ ማስከበር ስራ ሲሰሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት እንደተገደሉ፣ የጦር መሳሪያዎቻቸው እንደተወሰደባቸው እና የአካል መጉደል ጉዳት የደረሰባቸው አባላት እንደነበሩ ለችሎቱ መመስከራቸው ተገልጿል።
በቀጣዮቹ ቀናትም አቃቢ ህግ በተከሳሾቹ ቅስቀሳ የደረሱ ጉዳቶችን ለችሎቱ ያስረዱልኛል የሚላቸውን ተጨማሪ ምስክሮች እንደሚያቀርብ ጠበቃ ሰለሞን አክለዋል።
በእነ ክርስቲያን ታደለ መዝገብ ስር ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች በአቃቢ ህግ የተመሰረተባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ በወቅቱ ለችሎቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል።