
በገዳሙ ውስጥ ከሴቶች ጋር በሚኖርበት ወቅት ወንድነቱ እንዳይታወቅበት ከባድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል
ለ22 ዓመት ሴት መስሎ በሴቶች ገዳም ውስጥ የኖረው ሰው
ፍራንክ ታቫሬስ የዶምኒካን ሪፐብሊክ ሲሆን እናት እና አባቱን በትራፊክ አደጋ ምክንያት ገና በህጻንነቱ ነበር ያጣው፡፡ ተንከባካቢ ቤተሰብ ያጣው ይህ ህጻንም በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ የሴቶች ገዳም ያመራል፡፡
በገዳሙ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አንዲት እናትም ወላጆቹ የሞቱበት እና የሚንከባከበው ሰው እንደሌላ በመረዳት አብረውት እንዲኖር ይፈቅዱለታል፡፡
ረጅም ጸጉሩ አፍንጫው እና የፊቱ ቅርጽ የሴት መልክ የሰጠው ይህ ሰውም በገዳሙ ውስጥ ያስጠለሉት ህጻን ልጅ ጾታው ወንድ መሆኑን እንደማያውቁም ተናግሯል፡፡
ሲስተር ማርጋሪታ በሚል ስም የሚጠራው ይህ ሰው ከትንሽ ጊዜ በኋላ ህጻኑን ያስጠለሉት እናትም ህይወታቸው ማፉን ተከትሎ ይህ ሰው ህይወቱን ከሌሎች የመነኑ ሴቶች ጋር እንዲኖር ይደረጋል፡፡
ከሴት መናኞች ጋር በገዳም ውስጥ ህይወቱን የቀጠለው ይህ ሰውም እያደገ ሲመጣ ወንድ መሆኑን እንዳያውቁበት ሰፋፊ ልብሶችን መልበስ፣ የወር አበባ ህመሙ እንደበረታበት እና ሌሎች የማስመሰል ድርጊቶችን ሲያደርግ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም በገዳሙ ውስጥ አብራው ከምትኖር እና ሲስተር ሲለቪያ ተብላ ከምትጠራ መናኝ ጋር ፍቅር እንደያዘው ተናግሯል፡፡
ሲስተር ሲልቪያም እውነተኛ ማንነቱን ስታውቅ የፍቅር ጥያቄውን ተቀብላው ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ እያለ እርግዝና ይፈጠራል፡፡
ከእርግዝናው በኋላ የህይወቴ ምስቅልቅል ተጀመረ የሚለው ይህ ሰው እሷ ከገዳሙ እንውጣ ፣ ስራ እንፈልግ፣ ልጃችንንም እናሳድግ የሚል ጥያቄ ብታቀርብለትም ጥያቄውን ሳይቀበል እንደቀረ ተናግሯል፡፡
ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከገዳም ወጥቶ ወንድነቱን ተቀብሎ ስራ መጀመሩን የሚናገረው ይህ ሰው ሲልቪያ ግን ከልጇ ጋር ወደ አሜሪካ መጓዟን ኦዲቲ ሴንትራል የዶምኒካ ብዙሃን መገናኛዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ሲልቪያን ካጣበት ጊዜ ጀምሮ በኋላ ብቻውን እየኖረ መሆኑን የሚናገረው ይህ ሰው አሁን ላይ የ73 ዓመት አዛውንት የሆነው ሲሆን ከሲልቪያ ጋር ጣፋጭ እና የማይረሳው የፍቅር ጊዜ አሳልፌያለሁ ብሏል፡፡