ቱርክ የፕሬዝደንት ኢርዶጋንን ዋና ተቀናቃኝ አሰረች
ኢማሞግሉ በኤክስ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ተስፋ እንደማይቆርጡና ለሚደረግባቸው ጫና ሸብረክ እንደማይሉ ተጽፈዋል

የኢስታንቡል ገዥ ቢሮ በከተማዋ ሁሉም ስብሰባዎች እና ተቃውሞዎች እንዳይካሄዱ ለአራት ቀናት የሚቆይ እግድ አስተላልፏል
ቱርክ የፕሬዝደንት ኢርዶጋንን ዋና ተቀናቃኝ አሰረች።
የቱርክ ባለስልጣናት የፕሬዝደንት ኢርዶጋን ዋና ተቀናቃኝ የሆኑትን በሙስናና እና የሽብር ቡድንን በመርዳት በመክሰስ ዋና ተቃዋሚው "በቀጣይ ፕሬዝደንት ላይ የተፈጸመ መፈንቅለ መንግስት" ሲል የገለጸውን እስር በዛሬው እለት ፈጽመዋል።
የሪፐብሊካን ፕፕልስ ፓርቲ(ሲኤችፒ) አባል የሆኑት የኢስታንቡል ከንቲባ ኢክረም ኢማሞግሉ የሽብር ድርጅትን በመምራት፣ በጉቦና ጨረታ በማጭበርበር ክሶች ሁለት የተለያዩ ምርመራዎች ተከፍተውባቸዋል።
የኢማሞግሉ ፓርቲ ቱርክን ከሁለት አስርት አመታት በላይ የመሩት ፕሬዝደንት ኢርዶጋን ተፎካካሪ አድርጎ ሊሰይማቸው ጥቂት ቀናት ነበር የቀሩት። ለሁለት የስልጣን ዘመን የኢስታንቡል ከንታባ የሆኑት ኢማሞግሉ ወደፊት በሚደረግ ምርጫ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢማሞግሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ተስፋ እንደማይቆርጡና ለሚደረግባቸው ጫና ሸብረክ እንደማይሉ ተጽፈዋል።
የኢስታንቡል የአቃቤ ህግ ቢሮ የመጀመሪያ ምርመራውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኞችና ነጋዴዎችን ጨምሮ 100 ሰዎች ማዘጋጃ ቤት ከሰጠው ጨረታ ጋር በተያያዘ የወንጀል ተግባር ተሳትፈዋል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ጠቅሷል።
ቢሮው በሁለተኛ ምርመራው ኢማሞግሉ በቱርክና በምዕራባውያን አጋሮቿ በሽብር የተፈረጀውን የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲን (ፒኬኬ) ይረዳሉ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ከንቲባው የታሰሩት የኢስታንቡል ዩኒቨርስቲ ዲግሪያቸውን ውድቅ ካደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፤ ዩኒቨርስቲ ውሳኔውን የሚያጸናው ከሆነ በፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ያደርጋቸዋል።
የኢስታንቡል ገዥ ቢሮ በከተማዋ ሁሉም ስብሰባዎች እና ተቃውሞዎች እንዳይካሄዱ ለአራት ቀናት የሚቆይ እግድ አስተላልፏል።