ኤርትራ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እንደማትገባ ገለጸች
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ “ጊዜ ያለፈበት” ሲሉ ተችትዋል

አዲስ አበባ አስመራን ለውስጥ ችግሮቿ ተጠያቂ ከማድረግ እንድትቆጠብም አሳስበዋል
ኤርትራ በትግራይ ክልል እና በሌሎች የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ትገባለች በሚል የሚቀርብባትን ክስ አስተባበለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ በኤርትራ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በደረጉት ማብራሪያ ሀገራቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማትገባ ተናግረዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀላፊዎች እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አስመራ እየቀረበባት ያለው ክስ ሀሰተኛ መሆኑን እንዲረዱላት ጠይቃለች፡፡
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ማብራርያ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፣ የኤርትራ የጦርነት ዝግጅት እና በኢትዮጵያ የባህር ወደብ ጥያቄ ዙሪያ አተኩሯል፡፡
የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በህዳር 2022 ግጭቱ ካበቃ በኋላ ወደ ኤርትራ ዓለም አቀፍ እውቅና ወደ ተሰጠው ድንበሮች እንዲዘዋወረ መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ጦሩ አሁንም በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገር ማንኛውም አካል ለውስጥ ችግር ኤርትራን ተጠያቂ ማድረግ የሚፈልግ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ውንጀላዎች የኤርትራና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ውድቅ ባደረጉት የቀድሞ የህወሓት አባላት እና በኤርትራ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ጥረት በሚያደርጉ አካላት የሚሰራጩ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነትን የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አድርጎ ስለሚመለከተው በዚህ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም ተብሏል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ባለው የውስጥ ግጭት ውስጥ የኤርትራ መንግስት ምንም አይነት ሚና የለውም ያለው መግለጫው ፤ ከዚህ በተቃራኒ ያሉ ውንጀላዎችን እና ክሶችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንደሚያደርግ አመላክቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራርያ በስፋት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ የተመለከተ ሲሆን ይህን ጥያቄ “ጊዜው ያለፈበት” ሲል ተችቷል፡፡
“ኢትዮጵያ በወታደራዊ አልያም በዲፕሎማሲያዊ አማራጭ የባህር ወደብ ባለቤት እሆናለሁ በሚል በምታቀነቅነው ጊዜው ያለፈበት እና የተዛባ ፍላጎት ኤርትራ ግራ ተጋብታለች” ነው የተባለው፡፡
በዚህ ረገድ ኤርትራ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንድታከብር ጫና እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
“ከትግራይ ክልል የፖቲካ አለመረጋት ጋር ተያይዞ የኤርትራ ስም ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ሲነሳ ተስተውሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ “ከትግራይ ክልል ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ አካላት ውሰጥ የኤርትራ መንግስት አንዱ ነው” ማታቸው ይታወሳል።
አቶ ጌታው በመግለጫቸው፤ “ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ከወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት እንዳሉ እናውቃለን” ብለዋል።
የኤርትራ ፍላጎት የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስትን ይወራል ብለው በሚሰጉበት ሰአት ትግራይን እንደ መሸሸጊያ መጠቀም አሊያም ጠንከር ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለው ካመኑ ከትግራይ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ ማማተር ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ኤርትራ በህወሓት የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ያለውን የውስጥ ሽኩቻ የማባባስ ፍላጎት የላትም ማለታቸው።
ምክንያቱም በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው የውስጥ ሽኩቻ ማባባስ በትግራይ ህዝብ ላይ አላስፈላጊ እና ሊወገድ የማይችል ስቃይ የሚያስከት መሆኑን አክለዋል።