በስፔን አንድ ተጫዋች በ1 ጨዋታ 2 ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናበተ፡፡
በአንድ ጨዋታ ሁለት ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው ተጫዋች ክሪስቶባል ማርኩዌዝ አስገራሚ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
አጋጣሚው የተከሰተው ከትናንት በስቲያ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በስፔን ሁለተኛ ዲቪዥን በፉዬንላብራዳ እና ዢሮና መካከል በተደረገ ጨዋታ ላይ ነው፡፡
የፉዬንላብራዳው አማካይ ክሪስቶባል ማርኩዌዝ የተጋጣሚው ቡድን ተጫዋች ላይ አደገኛ ጥፋት ፈጽሟል በሚል በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ይሰናበታል፡፡ አማካዩም የዳኛውን ውሳኔ በመቀበል ሜዳውን ለቅቆ ወደ መልበሻ ክፍል አመራ፡፡
እስካሁን ያለው አዲስ ያልሆነ የማያስገርም ክስተት ሲሆን አስገራሚው ድራማ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡
ማርኩዌዝ ከሜዳ ከተሰናበተ በኋላ ዳኛው ሜዳው ጠርዝ በሚገኘው ስክሪን የጥፋቱን ክብደት መላልሰው ተመልክተው ውሳኔያቸውን በመቀልበስ ተሰናባቹ ተጫዋች ከመልበሻ ክፍል ተጠርቶ ወደ ሜዳ ተመልሶ እንዲገባ ያደርጋሉ፡፡ ቀይ ካርዱን ሽረው ቢጫ ካርድም ያሳዩታል፡፡
ጨዋታው ከቆመበት ከመቀጠሉ በፊት ግን ክሪስቶባል ማርኩዌዝ ከዢሮናው አሌክስ ግራኔል ጋር ግብ ግብ ፈጥሮ ሁለቱም ቢጫ ካርድ ሲሰጣቸው ካርዱ ለክሪስቶባል ሁለተኛው ሆነና በድጋሚ ቀይ ካርድ ተመልክቶ በመጣ እግሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ ተገዷል፡፡
ክለቡ ፉዬንላብራዳ በተጋጣሚው 1 ለ 0 መሸነፉ ደግሞ ለተጫዋቹና ለክለቡ ሌላ የሚያበሳጭ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ