አፍሪካ የምግብ ዋስትናዋን እንዳታረጋግጥ ግጭት ዋንኛ ፈተና ሆኗል
አፍሪካ የምግብ ዋስትናዋን እንዳታረጋግጥ ግጭት ዋንኛ ፈተና ሆኗል
በአፍሪካ የምግብ ዋስትናና ስርአተ ምግብ ላይ ትኩረት በማድርግ በአፍሪካ ህብረት በተካሄደ ውይይት ላይ አህጉሪቱ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋግጥ በምታደርገው ጥረት ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮኖሚ ችግር ከፍተኛ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከነዚህ መካከል ደግሞ ግጭት እና አለመረጋጋት ዋነኛው ፈተና ነው በአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ጆሴፋ ሳኮ እንደሚሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሰሃራ በታች አፍሪካ ብቻ 239 ሚሊዮን ያክል ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ችግር ተጋልጦ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክኒያት ግጭት እንደሆነ ነው የተገለጸው።
አብዛኛው ህዝቧ በግብርና በሚተዳደርባት አፍሪካ በአህጉሪቱ ጥቅል ዓመታዊ ገቢም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ይሄው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ነው።
የመንግሥታቱን ድርጅት የ2030 ዘላቂ የልማት ግብ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን አጀንዳ 2063 ከግብ ማድረስ የሚቻለውም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑን በመግለፅ መንግስታት ሰላምን በማስፈን ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ኮሚሽነር ሳኮ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተመድ ምግብና እርሻ ድርጅትና ሌሎችም በመስኩ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች ታድመዋል። እነዚህ ድርጅቶች እና ለጋሽ ሀገራት ቦኮሐራም እና አልቃኢዳን የመሳሰሉ ጽንፈኛ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት የሳህል ቀጣና ብቻ ከመወሰን አልሸባብ እና መሰሎቹ ያሉበትን ምስራቅ አፍሪካንም በትኩረት ሊደግፉ ይገባል ሲሉም ሳኮ ጥሪ አቅረበዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጸር የሆነውን ግጭትን ለማስወገድ እና በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የግብርና ሚነስትር ሁሴን ተናግረዋል።
ለችግሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ መፍትሔ ማምጣት ካልተቻለ የምግብ ዋስትናን አለማረጋገጡ ደግሞ ሌሎች ቀውሶችን እየወለደ አፍሪካ ባለችበት ከመሽከርከር አዙሪት ካለመውጣት ባለፈ ለከፋ ችግር መጋለጧ እንደማይቀር የገለፁት ደግሞ የምግብና እርሻ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማሪያ ሳማዶ ናቸው።
በ2018 ከሰሀራ በታች አፍሪካ 19 ግጭቶችን አስተናግዷል። ይሄም በወቅቱ በመላው ዓለም ከነበረው አንድ ሶስተኛው ነው።
መንግሥታዊ መዋቅሮችን ማስተካከል፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን እና ቃልን ወደ ተግባር ለመለወጥ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የምግብ ዋስትና ዋና ጸር የሆነውን ግጭትን ለማስወገድ የአፍሪካ መሪዎች በትጋት መወጣት ያለባቸው የቤት ስራ መሆኑ በውይይቱ ተጠቁሟል።