የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጊኒቢሳው ገባ
በጊኒቢሳው ነገ የሚደረገውን ምርጫ ለመታዘብ በሳኦቶሚና ፕሪንሲፔ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፋኤል ብራንኮ የሚመራ የታዛቢ ቡድን መላኩን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
ቡድኑ ወደ ሀገሪቷ ሲገባ የህብረቱ የጊኒቢሳው ላይዘን ኦፊሰር አቀባበል ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
ምርጫው ነገ የሚካሄድ ሲሆን የህብረቱ የምርጫ ታዛኒቢም ፍትሐዊ ግልጽና ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱን ይታዘባል ተብሏል፡፡
ቡድኑ ወደ ስፍራዉ ያቀናው በሀገሪቱ መንግስትና በብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን ጥያቄ መሆኑንም ህብረቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡
የአጭር ጊዜ ታዛቢዎቹ በፈረንጆቹ እስከ ጥር 2 ቀን እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን ሁሉንም ሂደት የሚታዘቡት ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ቀናት በጊኒቢሳው ይቆያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም የመርጫው አመራርና ውጤት ይፋ የማድረግ ሂደትን ለመታዘብ ያስችላል ተብሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ህብረት አመራሮች ከሀገሪቱ ባለድርሻ ጋር ውይይት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የህብረቱ ተዛቢዎች ትናንትና በአገሪቱ በሚገኙ 9 ክልሎች ተሰማርተዋል ፡፡ የልዑክ ቡድኑ አባሎች ወደ ክልሎቹ የተሰማሩት የቅድመ ምርጫ ሂደትንና እንቅስቃሴን ለመታዘብ እንዲሁም ለምርጫ ያለውን ዝግጅት ለመቃኘት መሆኑን ህብረቱ አስታውቋል፡፡
ልዑክ ቡድኑ እንዳለው ከሆነ ምርጫ ከተደረገ ከሁለት ቀናት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ከዚያ አስቀድሞ ግን ከምርጫው መካሄድ አንድ ቀን በኋላ ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች የተንቀሳቀሱት ታዛቢዎች በታዘቧቸው ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዴሞክራሲን ለማስፋፋትና ለማስተዋወቅ በማሰብ ነው ወደ ሀገሪቷ የገባው ተብሏል ፡፡
የታዛቢ ቡድኑ 13 የረጅም ጊዜ እንዲሁም 40 የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን ያካተተ ነው፡፡