በኬንያ በአልሸባብ ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ሶስት መምህራን ተገደሉ
በኬኒያ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ዛሬ ጥር 04 ቀን 2012 ዓ.ም አልሸባብ ሳይፈፅመው እንዳልቀረ በተገመተ ጥቃት ሶስት መምህራን መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጋሪሳ በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት ላይ በተከፈተው በዚሁ የተኩስ ጥቃት አንድ ተማሪም ቆስሏል፡፡ በተጨማሪም ታጣቂዎቹ በት/ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝን የፖሊስ ጣቢያ ያቃጠሉ ሲሆን የቴሌ መሰረተ ልማትም ማውደማቸው ተገልጿል ፡፡
ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱ ፖሊስ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ባደረገው የተኩስ ልውውጥ በጋሪሳ አራት ህፃናት መገደላቸው ይታወሳል፡፡
በኬንያ የሚገኘው የአሜሪካ ጦርም በላሙ ግዛት በታጣቂው በደረሰ ጥቃት ሶስት ወታደሮቹ መገደላቸውን ተከትሎ በስፍራው ጦሩን አጠናክሯል፡፡
ኬንያ ከ2011 ጀምሮ ጦሯን ወደ ሶማሊያ መላኳን ተከትሎ በአልሸባብ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሰለባ ሆናለች፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ