ክለቡ 2 ጨዋታ እየቀረው ነው ለ8ኛ ተከታታይ ጊዙ የቡንደስሊጋ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው
ባየርን ሙኒክ ለ8ኛ ተከታታይ ጊዙ የቡንደስሊጋው ባለድል ሆነ
ባየር ሙኒክ ትናንት ወርደር ብሬመንን ከሜዳው ዉጭ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለ8ኛ ተከታታይ ጊዙ የቡንደስሊጋው ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ሮበርት ለዋንዶውስኪ በ43ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ብቸኛው የጨዋታው ጎል ሙኒክ 11 ተከታታይ ጨዋታዎችን በድል እንዲያጠናቅቅ ከማድረግም ባለፈ 2 ጨዋታዎች እየቀሩት ዋንጫውን እንዲያሸንፍ አድርጋለች፡፡ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለዋንዶውስኪ የትናንትናዋ ጎል 31ኛው የሊግ ጎሉ ነች፡፡
ሙኒክ 32 ጨዋታዎችን አድርጎ 76 ነጥብ በመሰብሰብ 2ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በ10 ነጥብ ይበልጣል፡፡
የባየርን ሙኒክ ተጫዋቾች ሊጉን በድል ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ በባዶ ስታዲየም ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ እስካሁን ክለቡ ያሸነፋቸው የሊግ ዋንጫዎች (ከቡንደስ ሊጋ በፊት የነበረውን 1 ዋንጫ ጨምሮ) 30 ደርሰዋል፡፡ የቢቢሲ መረጃ እንደሚያሳየው ከአውሮፓ ምርጥ 5 ሊጎች በዋንጫ ብዛት ክለቡ የሚበለጠው በጁቬንቱስ (35 የሴሪ አ ዋንጫ) እን በሪያል ማድሪድ (33 የላ ሊጋ ዋንጫ) ብቻ ነው፡፡
የባየርን ሙኒክ አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በክለቡ ታሪክ በአሰልጣኝነት እና በተጫዋችነት የቡንደስሊጋ ዋንጫን ያነሳ ሶስተኛ ሰው ነው፡፡
ዴቪድ አላባ እና ቶማስ ሙለር 9 ጊዜ የቡንደስሊጋ ዋንጫ አሸናፊ በመሆን ባለፈው ዓመት በፍራንክ ሪቤሪ የተያዘውን ክብረወሰን ተጋርተዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለ 2 ወራት ተቋርጦ ዳግም የጀመረው የጀርመን ሊግ ሊጠናቀቅ ገሚሱ ክለቦች 2 ወዋታዎች ሲቀሯቸው የተቀሩት ደግሞ 3 ጨዋታዎች ይቀሯቸዋል፡፡