በምስራቅ አፍሪካ አምበጣን ለመከላከል ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን 10 ሚሊዮን ዶላር ለገሰ
በምስራቅ አፍሪካ አምበጣን ለመከላከል ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን 10 ሚሊዮን ዶላር ለገሰ
የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በምስራቅ አፍሪካ የበረሀ አምበጣ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል 10 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል፡፡ ገንዘቡ ለተባበሩት መንግስታት ምግብና እርሻ ድርጅት ፋኦ (FAO) የሚሰጥ ነው፡፡
የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ቁ ዶንግዩ ፋውንዴሽኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሌሎች አካላትም ወረርሽኙን ለመከላከል አፋጣኝ ድጋፍ በማድረግ ምስራቅ አፍሪካን ከርሀብ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡
ይቢል ጌትስን ድጋፍ ጨምሮ የመንግስታቱ ድርጅት እስካሁን 33 ሚሊዮን ዶላር በድጋፍ አሰባስቧል፡፡ ይሁንና በቀጣናው አምበጣን ለመከላከል ባጠቃላይ የሚያስፈልገው ገንዘብ 138 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ከወር በፊት 76 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሎ የነበረው የተባበሩት መንግስታት፣ አሁን ላይ የአምበጣ መንጋው መስፋፋቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከፍ አድርጎታል ብሏል፡፡
የበረሃ አንበጣዎች በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚገኙ ስድስት አገሮችን በመውረር ሰብሎችን እየበሉ ይገኛሉ ፡፡
የአምበጣ ወረራው ኬንያ በ 70 ዓመታት ውስጥ ያጋጠማት እጅግ አስከፊ ወረራ ሲሆን በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ደግሞ በ 25 ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋው ነው፡፡
አንድ ካሬ ኪ.ሜ የሚሸፍነው አንድ አነስተኛ የአምበጣ መንጋ በአንድ ቀን ውስጥ ከ 35,000 ሰዎች ጋር ተመሳሳይ መጠን ያለው ምግብ መመገብ ስለሚችል አንበጦች በቀጣናው ለምግብ ዋስትና ትልቅ ስጋት ናቸው ተብሏል፡፡
አንበጦች አመቺ የአየር ሁኔታ ሲኖር በፍጥነት የሚራቡ በመሆናቸው በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ 500 ጊዜ ያህል ሊባዙ ይችላሉ ፋኦ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፡፡