ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርትን በጊዜያዊነት ሊያቆም ነው
ቦይንግ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርቱን ከጥር ጀምሮ በጊዜያዊነት ሊያቋርጥ መሆኑን ገልጿል።
ኩባንያው የአውሮፕላን ምርቱ እንዲቆም ውሳኔ ያሳለፈው የቦርድ አባላቱ ለሁለት ቀናት በአሜሪካ ቺካጎ ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡
ይህ የሆነውም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ተመልሶ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይበራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የአሜሪካ አቪየሽን ተቆጣጣሪ ከአውሮፓውያኑ 2020 በፊት አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ እንዲገቡ ፍቃድ አልሰልጥም ማለቱን ተከትሎ ነው።
የቦይንግ ምርት በሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ በደረሰ አደጋ በድምሩ የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትትሎ ካሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ አውሮፕላኖቹ ከአገልግሎት ውጭ ተደርገው መቆማቸው ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ኩባንያው እስከ 9 ቢሊየን ዶላር አጥቷል ነው የተባለው።12 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ኩባንያው ከ737 ማክስ ጋር በተያያዘ ሰራተኞቹን እንደማይቀንስ አስታውቃል፡፡ሆኖም የኩባንያው ምርት ማቆሙ የእቃ አቅራቢ ድርጅቶችን እና አጠቃላይ የአሜሪካን ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሏል።
ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖችን ምርት ቢያቋርጥም፤ ለወታደራዊ ግልጋሎት የሚውለውን የP8 ስሪት ምርቶችን ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የቦይንግ አክሲዮን ገበያው እየተቀዛቀዘ ነው የተባለ ሲሆን፥ የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ምርትን ለጊዜያዊነት አቋርጣለሁ ማለቱን ተከትሎ የአክሲዮን ገበያው በ4 በመቶ መቀነሱ ነው የተነገረው።
ምንጭ፦ ሮይተርስ