አየር ንብረትን የተመለከቱ 5 ቀዳማይ ጥያቄዎች
የአየር ንብረት ለውጥና ተጽዕኖዎቹ አሁንም በአነጋጋሪነታቸው መቀጠላቸው አልቀረም፡፡ ጉዳዩ በመላው ዓለም ሊደቀን የሚችል ጣጣን የሚያመጣ በመሆኑም የብዙዎችን ቀልብ ገዝቷል፡፡ መሪዎች፣ተመራማሪዎች ያገባናል የሚሉ አካላትም ሁሉ ስለ ጉዳዩ ያላሳሰቡበት ጊዜ የለም፡፡ ይህንኑ ከግምት ውስጥ ያስገባው ሲቢኤስ ኒውስም ታዲያ ጉዳዩ አሁንም እያነጋገረ ብዙ ብዙ እየተባለለትም መቀጠሉ አይቀርም ብሏል፡፡ በተቋሙ የአየር ትንበያ ዘጋቢው ጄፍ ብራርዴሊ ታዲያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ሊነሱ እንደሚችሉ የገመታቸውን 5 ቁልፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮችን ከነመልሳቸው እንደሚከለው አስቀምጧል፦
1. የአየር ንብረት ለውጥን ልናቆመው አዳዲስ ፈጠራዎች ሊያግዙን ይችላሉን?
መልሱ አዎ ለውጡንና ተጽዕኖዎቹን ልናስቆም የምንችልባቸው አጋጣሚዎች አሁንም አሉ ነው፡፡ ሆኖም ይህ በቀላሉ ሊመጣ የሚችል እንዳይደለ ሲቢኤስ በዘገባው ያትታል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የበይነ መንግስታት የአየር ንብረት ፓናል ለውጡን ለማስቆም ከፈለግን እኤአ በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀታችንን በ45 በመቶ ቀንሰን የዓለምን የሙቀት መጠን ልኬት 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ማድረስ እንዳለብን ቢያሳስብም ይህ ግን ሊሆን የሚችል አይመስልም፡፡ የመሳካት እድሉም አናሳ ነው፡፡ሆኖም የተቀመጠው ልኬት ላይ ለመድረስ ባይቻልም እንኳን ለመጠጋት ግን ይቻላል፡፡ለዚህም የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ለውጡን መዋጋትን የስራ ዕድል ምንጭ ማድረጉ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሃብትን እገነባለሁ የምትለው ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ቀዳሚ ትኩረት መስጠቷም የዚሁ አካል ነው፡፡
2. የአየር ንብረት ለውጡ ይበልጥ ሊባባስ የሚችልባቸው የዓለማችን አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
የዘርፉ ምሁራንና ተመራማሪዎች ዓይናቸውን የማይነቅሉባቸው 3 ቀዳሚ ስፍራዎች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
ሀ). ጥቅጥቅ ዝናባማ የአማዞን ደኖች
11 የደቡባዊ አሜሪካ ሃገራትን የሚያካልለው ይህ ጥቅጥቅ ደናማ ስፍራ 7 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አለው፡፡ በብዝሃ ህይወት ይዞታውና ለአየር ንብረት ሚዛናዊነት ባለው የጎላ አበርክቶ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም አሁን አሁን የሚስተዋሉ የጭፍጨፋና ሌሎችም ተያያዥ ድርጊቶች የደኑን ይዞታ ችግር ላይ ሊጥሉት እንደሚችሉ እየተነገረ ነው፡፡በቅርቡ ሰደደ እሳት አጋጥሞት እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ለ). ፔርማፍሮስት-ግግሩ የአርክቲክ በረዶ
የአርክቲክ መደብ ስለመሆኑ የሚነገርለት ፔርማፍሮስት አሁን አሁን እየቀለጠ መሆኑ ይነገራል፡፡በዚሁ ምክንያት ለበርካታ ዓመታት አምቆት የኖረውን ካርቦን እየለቀቀ ስለመሆኑም ነው ሳይንቲስቶች የሚናገሩት፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ የዓለምን የሙቀት መጠን የሚጨምር ነው፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታት አነጋጋሪ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ ፔርማፍሮስት የሚቀልጥበት ፍጥነት ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
ሐ). የግሪንላንድ ደሴት እና በረዷማ የደቡባዊ ዋልታ አካባቢዎች
በአርክቲክ በግሪንላንድ እና በደቡባዊ የዓለማችን ዋልታ የሚገኘው ግግር በረዶ መቅለጥ የባህር ወለልን እና የውቅያኖሶችን ጥልቀት ከፍ እያደረገው ነው፡፡ የሙቀት መጠንን ሚዛናዊነት በመጠበቅ እና መሬትን በማቀዝቀዝ የማይተካ ሚና ያለው ይህ በረዷማ የመሬት ክፍል መቅለጥም ይዞት ሊመጣ የሚችለው ጣጣ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
3. የአየር ንብረት ለውጡ ምን ዓይነት ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?
የአየር ንብረት ለውጥ በእያንዳንዱ ኪስ ሊገባ የሚችል ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ይነገራል፡፡ የሲቢኤስ ዜና ሪፖርተሯ ካርተር ኢቫንስ በወርሃ ህዳር ዘገባዋ የኒዮርክ ኢንሹራንስ ካምፓኒዎች ለሰደድ እሳትና ለተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ዋስትና ለመስጠት አንገራግረው እንደነበር ጠቁማለች፡፡ ይህ ምናልባትም ለውሃማ አካላት የቀረቡ መኖሪያ ቤቶችን ጭምር ሊያካትት ይችላል፡፡
4. ተጽዕኖውን በተመለከተ በወጣቱ ትውልድ ያደረው ምኞት ወደ ፖሊሲ ሊቀየር ይችል ይሆን?
ተስፋ የሚሰጠኝ ይህ ነው ይላል ጄፍ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ራሱን የጉዳዩ አካል ማድረግ መጀመሩን ይገልጻል፡፡ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ስለ ጉዳዩ የሚብሰለሰሉ ወጣቶች ተግኝተዋል፤ በባለፉት 30 ገደማ ዓመታት ያልተቻለውን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አድርገው ብዙዎችን ለማነቃነቅ የቻሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አቀንቃኝ ወጣቶች ተፈጥረዋል የሚለው ጄፍ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አስቡት ሲልም ያስቀምጣል፡፡
5. የትኞቹ ተጽዕኖዎች ይበልጥ ዜጎችን ያስጨንቃሉ?
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ይበልጥ ምን ሊያሰጋቸው እንደሚችል ብዙዎችን ጠይቄያለሁ የሚለው ጄፍ ፍልሰት እና ስደት የሚሉ ሁለት ቀዳሚ ምላሾችን አግኝቻለሁ ይላል፡፡ በመልሶቹም ይስማማል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚያጋጥም የሙቀት መጨመር ምክንያት በረሃማነትና ድርቅ ተበራክቷል፡፡ ምርት ይታፈስባቸው የነበሩ የእርሻ ማሳዎች ወደ ባድማ ተቀይረው በረሃማነት ውጧቸዋል፡፡ ምናልባትም ይላል ጄፍ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ ለምድር ወገብ በሚቀርቡ አካባቢዎች መኖር እጅግ ሊያዳግት ይችላል፡፡ ይህ ብዙዎችን ሊያፈናቅል ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ሊያደርግም ይችላል፡፡ ነገሩ አሁን ተከስቶ እየተመለከትን ነው በሚል የሚናገሩ ሳይንቲስቶችም አልታጡም፡፡ ይህ ኣለም አቀፍ መልክ ሲይዝ ደግሞ እጅግ የከፋ ሰብኣዊ ድቀትን ሊያስከትል እና ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጣ እንደሚችል ሜቲዮሮሊጂስቱ ጄፍ አስቀምጧል፡፡
ምንጭ፡- ሲቢኤስ ኒውስ