ስለገዳይነቱ የሚነገርለት አዲሱ የቻይና ቫይረስ ምንድነው?
ኮሮና የተሰኘውና በማዕከላዊ ቻይና ውሃን ከተማ የተከሰተው አዲስ ቫይረስ 6 ሰዎችን ስለመግደሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች በኩል ከቻይና የሚወጡ ቫይረሱን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከሆነ 224 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል 219ኙ በቻይና የተጠቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በጃፓን (1)፣ በታይላንድ (2) እና ደቡብ ኮሪያ (1) ሪፖርት የተደረጉ ናቸው፡፡ከ224ቱ ውስጥ 217ቱ በምርመራ ሲረጋገጡ 17ቱ ግን በጥርጣሬ ደረጃ የተያዙ ናቸው፡፡
ለመሆኑ ይህ ኮሮና የተሰኘው አዲስ ቫይረስ ምንድነው? በምንስ ይተላለፋል? አል ዐይን አማርኛ ተከታዩን ዝርዝር ዘገባ አጠናቅሯል፡፡
የቫይረሱ ምንነት
ኮሮናቫይረስ (2019 nCoV) ቀላል ሊባል ከሚችለው ጉንፋን ጀምሮ ትኩሳትና በሳል ሳልን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ከባድ የመተንፈሻ አካል ክፍል ችግሮችን ሊያደርሱ ከሚችሉ ለሳምባ ምች አጋላጭ የቫይረስ ዓይነቶችም ይመደባል፡፡በኤሽያ 800 ገደማ ሰዎችን ገድሎ የነበረው እና ሳርስ የተሰኘው የሳምባ ምች በሽታ ተመልሶ መጥቶ ይሆን ሲሉም ራሽያን ታይምስን መሰል አንዳንድ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ቫይረሱ ከስርዓተ ትንፈሳ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚያትተው የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነም ሚድል ኢስት እና ሳርስ ተብለው እስከሚጠሩ የሳንባ ምች ዓይነት በሽታዎች ሊደርስ የሚችል የጤና መታወክን ያመጣል፡፡
መተላለፊያ መንገዶች
ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ በርካታ የቫይረስ ዓይነቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ሚድል ኢስት ተብሎ የሚጠራው የሳምባ ምች ዓይነት ከግመል፤ሳርስ ደግሞ ከጥርኝ ይመጣሉም ነው የሚባለው፡፡ ኮሮናቫይረስም ሰውን ያጠቃል ተበብሎ አይታሰብም ነበር፡፡ አሁን ግን ከእንስሳት ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ የቫይረስ ዓይነት (Zoonatic) እንደሆነ ነው WHO ያስታወቀው፡፡
በወርሃ ታህሳስ መገባደጃ አካባቢ ተከስቶ ብዙዎችን ያጠቃውን የመተንፈሻ አካል ችግር ምንነት በውል ለማወቅ ያልቻለው የድርጅቱ የቻይና ማስተባበሪያ ጽ/ቤትም የሳምባ ምች ሊሆን እንደሚችል ነበር ያስቀመጠው፡፡ ሆኖም የቻይና ባለስልጣናት መንስዔው አዲስ የተከሰተና የመተንፈሻ አካል ክፍልን የሚጠቃ ቫይረስ እንደሆነ ከ15 ቀናት በፊት ደርሰውበታል፡፡
ምልክቶች
ለመተንፈስ መቸገር፣ትኩሳት፣ሳል የቫይረሱ ምልክቶች ናቸው፡፡ ቫይረሱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ሲደርስ እስከ ሳምባ ምች፣ የኩላሊት አለመስራትና እስከ ሞት ሊያደርስም ይችላል፡፡
ቫይረሱ ተላላፊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ የተለየ ምልክት የሚታም ከሆነ መታከም የሚገባ ሲሆን የአፍና አፍንጫ አካባቢ መሸፈኛ (ማስክ) መጠቀም ንክኪንም መቀነስ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት
በቻይና ሪፖርት ከተደረጉት 219 ኬዞች ውስጥ 198ቱ ከውሃን፣5ቱ ከቤጂንግ 14ቱ ደግሞ ከጉዋንግዶንግ ግዛት ሪፖርት የተደረጉ ናቸው፡፡ ከተጠርጣሪ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከልም በሲሹዋን 2፣ በዩናን 1፣ በሻንጋይ 2፣ በግዋንግዢ ዥዋንግ ራስ ገዝ አስተዳደር እና በሻንዶንግ ግዛቶችም በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ይገኛሉም ተብሏል፡፡ 15 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ስለመያዛቸውም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ቫይረሱንና ስርጭቱን አስመልክቶ አዳዲስ መረጃዎችን ባሰፈረበት ጽሁፉ አስነብቧል፡፡
በከፍተኛ የሳምባ ምች አጋላጭነቱ የሚጠቀሰውን ይህን ቫይረስ ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥብቅ እርምጃዎችን በመውሰድ ጭምር እንደምትሰራም ቻይና አስታውቃለች፡፡
የሃገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት አጸፋ
WHO ሃገራት እንዴት ቫይረሱን እንዴት ሊከላከሉ እንደሚችሉ ዘርዝር መረጃዎችን አውጥቷል፡፡እንዴት መለየት፣መመርመር እና ማከም እንዲሁም ግንዛቤን ማስጨበጥ እንደሚቻልም አስታውቋል፡፡ሆኖም ቫይረሱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ ጉዞዎች ይቋረጡ አይቋረጡ ስለሚለው ጉዳይ የሰጠው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሃገራት ጥንቃቄን እንዲያደርጉና የአደጋ ጊዜ ዝግጅት እንዲኖራቸው ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል፡፡
ቫይረሱ ዓለም አቀፍ የጤና የአደጋ ጊዜ አዋጅን ይፈልግ አይፈልግ እንደሆነ ለመወሰንም የWHO ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከፍተኛ ባለሙያዎቻቸውን ነገ ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡በስብሰባው ቫይረሱንና መከላከያ መንገዶቹን የተመለከቱ ምክረ ሃሳቦች እንደሚቀርቡ ዶ/ር ቴዎድሮስ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣አሜሪካ፣ጃፓን፣ሆንኮንግ እና ሲንጋፖርም ውሃንን ጨምሮ ከተለያዩ የቻይና ግዛቶች ወደ ሃገራቸው የሚገቡ መንገደኞችን እየመረመሩ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡