በብዙዎቹ የቀጣናው ሃገራት ሰዓት እላፊ እየታወጀ ነው
በመካከለኛው ምስራቅ ሰዓት እላፊ እየታወጀ ነው
የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በሚል የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ሰዓት እላፊን እያወጁ ነው፡፡
ጠበቅ ያሉ የቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ተሰምቷል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሰዓት እላፊን አውጃለች፡፡ አዋጁ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት ይተገበራል የተባለ ሲሆን ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ማለዳ 12 ሰዓት ድረስ ማንም መንቀሳቀስ እንደማይችል ንጉስ ሳልማን አውጀዋል፡፡
ከሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንደተገኘው መረጃ ከሆነ በሳዑዲ እስካሁን 511 ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ትናንት እሁድ ብቻም 119 አዳዲስ የኮሮና ኬዞች መገኘታቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡
ዜጎቿ ከቤታቸው እንዳይወጡ ከሳምንት በፊት ጀምራ የከለከለችው ሊባኖስ የክልከላውን ተግባራዊነት ለማረጋገጥና ለማስተግበር የመከላከያ ሰራዊት አባላቷንና የጸጥታና ደህንነት ሰዎችን አሰማርታለች፡፡
ጦሩ ቤሩትን ጨምሮ በሃገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በሄሊኮፕተር እየተዘዋወረም ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በማሳሰብ ላይ ይገኛል፡፡
ዜጎች የቫይረሱን መከላከያ ምክረሃሳቦች እንዲተገብሩ ያሳሰበው ጦሩ ኃላፊነቱን በማይወጡ ላይ ከፍ ያለ ቅጣትን እንደሚጥልም አስታውቋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም ጠንከር ያሉ ተመሳሳይ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
ዜጎች በቤታቸው እንዲቆዩ ከማዘዝ ባለፈ ለሁለት ሳምንታት ያህል በሃገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ገበያ አዳራሾች እንዲዘጉ ለማድረግ መወሰኗን አስታውቃለች፡፡
እስከዛሬዋ ቀን ማለትም እለተ ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ/ም በመላው ዓለም 3 መቶ 41 ሺ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 14 ሺ 7 መቶ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል፡፡