ኮሮና ቫይረስ እና ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሁለት የኢትዮጵያ ተቋማትን እያከራከሩ ነው
ኮሮና ቫይረስ እና ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሁለት የኢትዮጵያ ተቋማትን እያከራከሩ ነው
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አባላት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ (ኮሎኔል) እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቸው እየተነገረ ነው፡፡
በጃፓን መዲና ቶኪዮ የሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን በተመለከተ ሁለቱ የሃገሪቱ የስፖርት ተቋማት ለሁለት ተከፍለዋል፡፡
ሁለቱን ተቋማት ምን አጣላቸው?
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) የቶኪዮ ኦሎምፒክ በእርግጠኝነት እንደሚካሄድ እና ለዚህም አሰልጣኞች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በዓለም ከፍተኛ የጤና ሥጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አብዛኞቹ ውድድሮች በመሰረዛቸው አትሌቶች ዕድል አግኝተው ብሔራዊ ቡድን ላይ ያተኩራሉም ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ "በመጪው የሐምሌ ወር ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት አትሌቶች ሆቴል ገብተው መሰልጠን አለባቸው" ሲሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ደራርቱ ቱሉ ደግሞ "ከ100 በላይ አትሌቶቻችን በአንድ ሆቴል መግባት የለባቸውም" በሚል ሀሳቡን ተቃውማለች፡፡
ኮሎኔል ደራርቱ "የአትሌቶቹ ዝግጅት አካላዊ ንክኪ የበዛበት ነው፤ በዝግጅት፣ በምግብና በአውቶብስ እንቅስቃሴ ወቅትም ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸው የበዛ ነውም" ብላለች፡፡
"የኦሎምፒክ ኮሚቴው ሎጅስቲክስ ይመለከተዋል እንጂ እንደዚህ አይነት ውሳኔ መስጠት አይችልም፤ አትሌቶቹ ልጆቼ ናቸው፤ ባሉበት ልምምድ መስራታቸውን ይቀጥላሉ፤ እኔ የተቋም መሪ ነኝ እንጂ አሻንጉሊት አይደለሁም" ስትልም ኮሎኔል ደራርቱ ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን "በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ውድድሮችን ዘግቷል፣ እኔም ብሆን ስለ ውድድር ከማውራቴ በፊት ስለ ኮሮና ነው ማወራው፣ በመሆኑም አትሌቶች በአንድ ላይ ሆነው ሆቴል መግባት የለባቸውም" ብለዋል፡፡
አሁን ላይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን "አትሌቶች አንድ ሆቴል ይቀመጡና ልምምድ ይስሩ ማለት ለኮቪዲ 19 ቫይረስ ተጋላጭ መሆን ነው የሚል አቋም የያዘ ሲሆን፣ ኮሚቴው (የቶኪዮ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ) አትሌቶቹ አንድ ላይ ቢሆኑ ለጤናቸው የበለጠ ጥሩ ነው ብሏል፡፡
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን እና አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማሪያምን በአባልነት ያካተተው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አትሌቶቹ ሆቴል ገብተው መሰባሰብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት እሰጥ አገባ ውስጥ በገቡበት በዚህ ወቅት የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ የቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲራዘም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴም በጉዳዩ ላይ እየመከረ ሲሆን ካናዳ እና አውስትራሊያ በኦሎምፒክ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተቋማት ግን አሁንም ንትርክ ላይ ናቸው፡፡