ከመጠጥ ጋር ቁርኝት ያላቸው ወንዶች በሴቶች ላይ በብዛት ፆታዊ ጥቃት ያደርሳሉ ተባለ
መጠጥ አብዝተው የሚጠጡ ወንዶች ከሌሎች ወንዶች ስድስት ወይም ሰባት እጥፍ በትዳር አጋሮቻቸውና ሌሎች ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈፅሙ አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በስዊድን ሀገር ለ16 ዓመታት ከጤና ተቋማትና ከፖሊስ በተሰበሰበ መረጃ መነሻነት የተሰራ ነው፡፡
ከአሜሪካ፣ስዊድንና እንግሊዝ የተወጣጡ ሳይንቲስቶች በተሳተፉበት ጥናት ከአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ ጋር ተያይዞ ህክምና እየተደረገላቸው ባሉ 140 ሺ ወንዶች ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህም 1.7 በመቶ አልኮል አብዝተው የሚጠቀሙ ወንዶች በሴቶች ላይ ባደረሱት ጥቃት በፖሊስ ተይዘዋል 2.1 በመቶ አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ወንዶችም በተመሳሳይ ጥቃት ለእስር የተዳረጉ ናቸው፡፡
ይሄም መጠጥ አዘውታሪዎች ጤናቸውን ከመጉዳት ባለፈ ሌሎችን የመጉዳት እና ማህበራዊ ቀውስ የማድረሳቸው እድል የሰፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ጥናቱን የመሩት በኦክስፎር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሴና ፋዜል ግኝቱ በቤት ውስጥ የሚፈፀምን ፆታዊ ጥቃት ለመቀነስ የአልኮልና ዕፅ ማገገሚያ ህክምናን ማሻሻል እንደሚገባ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ