ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ እፈልጋለሁ አለች
የህዳሴ ግድብን ጉዳይ ግብጽ ወደ ጸጥታው ም/ቤት እወስዳለሁ ማለቷ ይታወቃል
ግብጽ የተለሳለሰ አቋም ያንጸባረቀችው በምን ምክንያት ነው?
ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ እፈልጋለሁ አለች
የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታ እንደምትፈልግ አስታወቁ፡፡ ግብጽ በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ ሲካሄድ የነበረውን ድርድር በማቋረጥ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደምትወስድ ስትገልጽ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ግን ካይሮ ይህንን የምታደርገው የዲፕሎማሲ ሂደቱን ለመጠቀም በማሰብ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ሀገራቸው በግድቡ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል ነው የተባለው፡፡ ካይሮ ጉዳዩን ባለፈው አርብ ዕለት ወደ ኒውዮርክ ለመውሰድ የወሰነችው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን እስከመጨረሻው ለመጠቀም በማሰብ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡
ፕሬዝደንቱ ሀገራቸው በግድቡ ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ፍላት እንዳላትም መናገራቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡
ግብጽ ትናንትና በፕሬዚዳንቷ በኩል ጦሯ ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ እንዲሆን ማዘዛቸው ይታወሳል፡፡ ይሔም በሊቢያ ከተፈጠረው ቀውስ እና ግብጽ የምትደግፈው የካሊፋ ሃፍታር ጦር በቱርክ በሚደገፈው እና የተባበሩት መንግስታት ዕውቅና ያለው የፋይዝ አልሳራጅ መንግስት ጦር በሚሰነዘርበት ጥቃት ክፉኛ እያፈገፈገ ከመሆኑ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡
ይሁንና ከግድቡ ጋር በተያያዘም ቢሆን ግብጽ የሀይል እርምጃም እስከመውሰድ እንደምትደርስ በተደጋጋሚ ይፋ አድርጋለች፡፡ አሁን ታዲያግብጽ በግድቡ ዙሪያ ዲፕሎማሲን አስቀድማለሁ የማለቷ ምክንያት ምናልባትም በሊቢያ ፖለቲካ ከቱርክ ጋር የገባችው አሰጥ አገባ ሊሆን እንደሚችል በብዙዎች ይገመታል፡፡
ከሰሞኑ የኢትጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከአሶሺየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀገራው ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰ ፣ የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት ስራዋን በዕቅዷ መሰረት እደምታከናውን ገልጸዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ግብጽ በግድቡ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ድርድር ካቋረጠች ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ዳግም ወደ ድርድር አትመለስም ማለታቸውም ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን ተጠቅማ ግድብ ከመገንባት የሚያግዳት ሃይል እንደሌለ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ግብጽ “ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል” የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ “ግብጽና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ” የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡