30ሺ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድን አግኝተው በየዩ.ኤ.ኢ ይኖራሉ
ለአህጉራዊ ትስስር ማሳያ ነው የተባለውን የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችን ምጣኔሃብታዊ ትብብር ለማጠናከር እየተሰራ ነው
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሱልጣን ቢን ሰይድ አል ማንሱሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በሁለቱ ሃገራት መካከል ባለው ምጣኔሃብታዊ ትስስር ዙሪያ ማተኮሩን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አስታወቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና የዩ.ኤ.ኢ የኢኮኖሚ ትብብር ከሃገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት ባሻገር የሁለት አህጉር ቀጠናዊ ትስስር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አል ማንሱሪ በበኩላቸው፥ በሃገራቱ መካከል እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ዩ.ኤ.ኢ አመታትን የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው
ይህ ግንኙነታቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ ከተባለበትና ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ከአቡዳቢው ልዑል አልጋወራሽና ከየዩ.ኤ.ኢ ጦር ኃይሎች ምክትል የበላይ አዛዥ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው፡፡
የሃገራቱን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ነው ሲሉም ነበር በዩ.ኤ.ኢ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሱሌይማን ዴደፎ እንደ አዲስ የተጠናከረውን የሃገራቱን ግንኙነት ከወራት በፊት ለ ’ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ’ የገለጹት፡፡
30ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድን አግኝተው በየዩ.ኤ.ኢ እንደሚኖሩና እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
የሃገራቱ ግንኙነት ከዚህም የተሻገረ ነው፡፡ በግብርና፣በመሰረተ ልማት፣በትምህርት፣በመኖሪያ ቤት ግንባታ እና በከተማ ልማትም በትብብር ይሰራሉ፡፡
ለዚህም ኤግል ሂልስ በተባለው የሪል ስቴት ገንቢ የየዩ.ኤ.ኢ ኩባንያ ይገነባል የተባለው ለገሃር የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና የከተማ ልማት ፕሮጄክት አንዱ ነው፡፡
በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብርም ይበልጥ ተጠናክሯል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ እና የቀንዱ አካባቢ ሰላም እንዲረጋገጥ በመተባበርም ረገድ ዩ.ኤ.ኢ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦን በማበርከት ላይ ናት፡፡