በደቡብ ክልል 5 ዞኖች የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ዛሬ ታህሳስ 07 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ፖሊዮ መሰል በሽታ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ በመታየቱ ለዚህ ወረዳ አጎራባች በሆኑ የደቡብ ክልል 5 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ከመጪው አርብ ታህሳስ 10 ጀምሮ ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና ስራ ሂደት ባለቤት አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንዳሉት በክትባቱ በኦሮሚያ ክልል ሲራሮና ሻላ ወረዳዎችም የሚካተቱ ሲሆን ለ4 ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በመጀመሪያው ዙር በደቡብ ክልል ሀዲያ፣ከንባታ ጠንባሮ፣ሀላባ፣ሲዳማና ወላይታ ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ 176ሺ ህጻናት ይሰጣል፡፡
በ2ኛ ዙር ደግሞ በሲዳማ ዞን ስር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ክትባቱ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ በአንድ የ24 ወር ህጻን ላይ ፖሊዮ መሰል በሽታ መታየቱን የገለጹት የስራ ሂደት ባለቤቱ የሴቶች ልማት ቡድን አባላትና የሀይማኖት አባቶች ዘመቻውን የማገዝ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ለዚህ የክትባት ዘመቻ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በቅንጅት እየሰሩ ነው ያሉት አቶ እንዳሻው ለዘመቻው ስኬት ትምህርት ቢሮዎች፣ሚዲያ፣የሲቪክ አደረጃጀቶችና ህብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ክትባቱ ከዚህ ቀደም ለተከተቡም ይሁን ላልተከተቡ ህጻናት የሚሰጥ መሆኑንም አቶ እንዳሻው አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ፡-የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ