ኢትዮጵያውያን በቻይና የተደረገውን የዢያሜን ማራቶን አሸነፉ
በትናንት እለት በቻይና በተደረገው የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች ማሸነፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ነው ያሸነፉት።
አትሌት መዲና ደሜ 2 ሰአት ከ26 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን በባለፈው ዓመት ውድድር በርቀቱ ያስመዘገበችውን የግል ምርጥ ሰአት በ1 ደቂቃ ከ13 ሴኮንድ አሻሽላለች።
አትሌት መዲና የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶንን ለሁለተኛ ቀን ተከታታይ ዓመት ማሸነፍ የቻለች ሲሆን ውድድሩን ለሁለት ጊዜ ያሸነፈች አራተኛዋ አትሌት ሆናለች።
አትሌት ፋቱማ ሳዶ፣አትሌት ማሬ ዲባባና ቻይናዊቷ አትሌት ዙ ቹንዢዩ የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶንን ሁለት ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ አትሌቶች ናቸው።
አትሌት መሰራ ሁሴን 2 ሰአት ከ26 ደቂቃ ከ28 ሴኮንድ ሁለተኛ፤ አትሌት አፈራ ጎድፋይ 2 ሰአት ከ26 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።
የትናንትናው ውጤት በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን ለ11ኛ ተከታታይ ዓመት ያሸነፉበት ነው።
በወንዶች ባለፈው ዓመት በዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን ሶስተኛ ደረጃ ወጥቶ የነበረው አትሌት ብርሃን ነበበው 2 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ የዘንድሮው ውድድር አሸናፊ ሆኗል።
ኬንያዊው አትሌት ሩበን ኬሪዮ 2 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን አትሌት ግርማይ ብርሃኑ 2 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በውጤቱ መሰረት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት በዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን በማሸነፍ የበላይነት መያዛቸውን የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል።
ለ18ኛ ጊዜ የተካሄደው የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
በሌላ በኩል ዛሬ በጣልያን በሚካሄደው የካምቺዮ አገር አቋራጭ ውድድር በ10 ኪሎ ሜትር ወንዶች አትሌት ለሜቻ ግርማ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል።
አትሌት ለሜቻ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በኳታር በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል በኬንያዊው አትሌት ኮንሰስሉስ ኪፕሩቶ በ0 ነጥብ 01 ማይክሮ ሴኮንድ ተቀድሞ የወርቅ ሜዳሊያውን ማጣቱ የሚታወስ ነው።
አትሌት ታደሰ ወርቁ በውድድሩ ላይ የሚሳተፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው።
የኬንያ፣ጣልያንና ስዊድን አትሌቶች የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በሴቶች የ6 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት አለሚቱ ታሪኩና አትሌት ፎተን ተስፋይ ይሳተፋሉ።