በኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት ጥንቃቄ ዝቅተኛ መሆኑን INSA አስታወቀ
በኢትዮጵያ ካሉ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ውስጥ 59 ነጥብ 5 ከመቶ የሚሆኑት ስልክ ቁጥርን እንደ ይለፍ-ቃል /password/ እንደሚጠቀሙ ጥናት አመለከተ።
ተጠቃሚዎች የስልክ ቁጥርን መጠቀማቸው ጠንካራ የይለፍ-ቃል እንደተጠቀሙ እንደሚሰማቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ መጠን እያደገ መምጣቱም ነው የተነገረው።
በኢትዮጵያ ያለው የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ መጠንም ዝቅተኛ እንደሆነ የኢንፎርሜሽን መረብና ደህንነት ኤጀንሲ ጥናት ያመለክታለል።
ኤጀንሲው በ2011 ዓ.ም 1 ሺህ 635 የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ሀገር-አቀፍ የሳይበር ደህንነት ምዘና ጥናት አከናውኗል።
በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 975 (59 ነጥብ 5 በመቶ) ያክሉ ስልክ ቁጥርን እንደ ይለፍ-ቃል/password/ በመጠቀም ጠንካራ የይለፍ-ቃል እንደተጠቀሙ እንደሚሰማቸው ጥናቱ ያመለክታል።
በተጨማሪም 59 ነጥብ 1 በመቶ ያክሉ የጥናቱ ተሳታፊዎች የይለፍ ቃሎቻቸውን የሚታይ ቦታ ላይ ጽፈው ማስቀመጥን እንደ ማስታወሻ መንገድ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።
67 ነጥብ 6 ከመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች ትክክለኛ ናቸው ብለው እንደሚያምኑም ነው የተነገረው።
በመሆኑም የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በቸልታ ሊታለፍ የማይገባውና የለት ተለት የህይወታችን አካል እየሆነ በመምጣቱ ተገቢውን ትኩረትና ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብና ደህንነት ኤጀንሲ የሰራውን ጥናት አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡