ጋና ከዳያስፖራ ዜጎቿ ከ3 ቢሊዬን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማሰባሰብ አቅዳለች
ጋና ከዳያስፖራ ዜጎቿ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ3 ቢሊዬን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማሰባሰብ አቅዳ ወደ ተግባር በመግባት ላይ ነች፡፡
የሃገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ኦፎሪ-አታ እንደተናገሩት ጋና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቿ ከ3 ቢሊዬን ዶላር በላይ ገንዘብን ለማሰባሰብ አቅዳለች፡፡
ገንዘቡ አፍሪካን ሳንኮፋ በተሰኘ አካውንት ተሰብስቦ ለተለያዩ የልማት ተግባራት እንደሚውል ኦፎሪ ተናግረዋል፡፡
መንግስት የኢንቨስትመንት መዋቅሩን ያሻሽላል ያሉት ሚኒስትሩ በውጭ ምንዛሬ ለሚቆጥቡ የተሻለ ወለድን ያስባል ብለዋል፡፡
ማሻሻያውን ለማምጣት በሚፈለገው ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ውስጥ ዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲኖረውና የተሻለ ተጠቃሚነትን እንዲያገኝ በማሰብ በሀገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ጋና እኤአ በ2017 1.6 ፣ በ2018 ደግሞ 2.5 ቢሊዮን ዶላር በሬሚታንስ መልክ አግኝታለች፡፡
እንደ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ ከሆነ ቁጥሩ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 2019 ከዚህ ተሻግሮ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ሊበልጥ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ሚኒስቴሩ በዕቅዱ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ከጋና ባንክ ጋር ተወያቶ አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ይፋ የማድረግ ውጥን እንዳለውም ኦፎሪ ተናግረዋል፡፡
ከዳያስፖራው የሚሰበሰበው ገንዘብ ለመሰረተ ልማት፣ለግብርና እድገት እና ቱሪዝም ልማት ይውላል ተብሏዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን