የአምናው ሻምፒዮን ሊቨርፑል በድምር ውጤት 4 ለ 2 ተሸንፎ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሰናበተ
የአምናው ሻምፒዮን ሊቨርፑል በድምር ውጤት 4 ለ 2 ተሸንፎ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሰናበተ
በሊጉ የመጨረሻ 16 ሁለተኛ ዙር ውድድር ትናንት ምሽት በአንፊልድ አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናገደው ሊቨርፑል 3 ለ 2 ተሸንፏል፡፡
መደበኛውን የጨዋታ ጊዜ ሊቨርፑል 1 ለ 0 ቢያጠናቅቅም፣ በመጀመሪያው ዙር በተመሳሳይ 1 ለ 0 በመሸነፉ በተሰጠው ተጨማሪ 30 ደቂቃ ባጠቃላይ 3 ለ 2 ተሸንፏል፡፡
በሁለቱ ዙሮች በድምር ውጤት 4 ለ 2 በመሸነፍ አምና የዋንጫው ባለቤት የነበረው ሊቨርፑል የመጨረሻ 8 ውስጥ መግባት ተስኖት ሊሰናበት ችሏል፡፡
ዋንጫውን ለ7ኛ ጊዜ ለማሸነፍ አኮብክቦ የነበረው ሊቨርፑል ከ43ኛው ደቂቃ የዊናልደም ጎል በኋላ በ94ኛ ደቂቃ ፈርሚንሆ ሁለተኛዋን ጎል ሲያስቆጥር ከሜዳው ውጭ በመጀመሪያው ዙር የገጠመውን የ 1 ለ 0 ሽንፈት እንደሚቀለብስ ታምኖ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሎሬንቴ በ 97ኛው እና 105ኛው ደቂቃ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ግቦች የሊቨርፑልን ተስፋ ያጨለሙ ነበሩ፡፡ በተመናመነ ተስፋ ውስጥ ሆነው ሊቨርፑሎች ተጭነው ሲጫወቱ በፈጠሩት ክፍተት ሞራታ በመጨረሻው የተጨማሪ ሰዓት ደቂቃ ሶስተኛ ጎል በማስቆጠር ክለቡ በአስተማማኝ ውጤት ድል እንዲነሳ አድርጓል፡፡
በርካታ የሊቨርፑል ሙከራዎችን ከግብ የታደገው የአትሌቲኮ ማድሪድ ግብ ጠባቂ ጃን ኦብላክ የጨዋታው ኮከብ ሆኗል፡፡
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጃርገን ክሎፕ የአትሌቲኮን በመከላከል የታጀበ አጨዋወት ተችተዋል፡፡ የተቆጠሩባቸው ጎሎችም የሚያስቆጩ መሆናቸውን የገለጹት ክሎፕ በቡድናቸው እልህ አስጨራሽ ጥረት ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሌላ የሸምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ፒኤስጂ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 2 ለ 0 በማሸነፍ በድምር 3 ለ 2 ውጤት ወደቀጣጡ ዙር አልፏል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ በዝግ ስታዲየም በተካሄደው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የፒኤስጂን ጎሎች ከእረፍት በፊት ኔይማር እና ቤርናት አስቆጥረዋል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ