በሶማሌ ክልል የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ
የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያሳየው ተነሳሽነት የሚያበረታታ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሩ በጅግጅጋ ከተማ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የመከሩ ሲሆን በተለያዩ እስር ቤቶች ተዘዋውረው ታራሚዎችን አነጋግረዋል፡፡
በጅግጅጋ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ሥር የሚገኘውና በተለምዶ ሀቫና በመባል የሚጠራው እስር ቤት የንፅሕና ደረጃ እና የእስረኞች አያያዝ ሊሻሻል ስለሚገባበት ሁኔታ ከኃላፊዎቹ ጋር የመከሩም ሲሆን እስረኞች ፖሊስ አደረሰብን ያሉትን አካላዊ ጥቃት ኮሚሽኑ ስልታዊ በሆነ መንገድ ክትትል ማድረጉን እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት፡፡
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሚያስገነባው አዲስ ማረሚያ ቤት በተለይ ጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው ፋፈን ማረሚያ ቤት የሚስተዋለውን መጨናነቅ ለማቅለልና የታራሚዎችን አያያዝ ለማሻሻል እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ተፈጽሞበታል በተባለው ድብደባ ሆስፒታል ገብቶ ሕይወቱ ያለፈው ወጣት-አዲስ መብራቱ- ጉዳይ የሚያሳዝን ነው ያሉት ዶ/ር ዳንዔል ኮሚሽኑ ጉዳዩን በዝርዝር እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ዳንዔል አያይዘው የክልሉ መንግስት ለእስረኞች መብት አጠባበቅና አያያዝ ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ያሉ ሲሆን ኮሚሽኑ ያደረገውን ማጣራት መሠረት በማድረግ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የተደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግን ስለመሆኑም ገልጸዋል ፡፡
ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መብት አጠባበቅን በተመለከተ የተገኘውን አበረታች ውጤት ለማስቀጠል ኮሚሽኑ አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታተል ዶ/ር ዳንዔል መናገራቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡