የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ተደራሽነት ላይ የሚሰራ ግብረ ኃይል ተቋቋመ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ተደራሽነት ላይ የሚሰራ ግብረ ኃይል ተቋቋመ
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኮሮና ወረርሽኝ ዙርያ የጤና ሚኒስቴር ተግባራትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እና የተቀናጀ ትክክለኛ የመረጃ አሰጣጥ እና ስርጭት እንዲኖር ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በወረርሽኙ ዙርያ መረጃ ሲሰጥ የነበረውን 8335ን በማጠናከር ከ36 በላይ የጥሪ መልስ የሚሰጡ የጥሪ ማዕከላትን በማዘጋጀት እና ከዚህ በፊት ለኤች አይ ቪ ኤድስ ትምህርት መስጫ የጥሪ ማዕከልነት ሲያገለግል የነበረውን 952ን ለኮሮና ቫይረስ መረጃና ትምህርት ሰጭ ማዕከልነት ለመጠቀምም እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ማንኛውንም አይነት ወረርሽኙን የሚመለከት መረጃን ህብረተሰቡ 444 ላይ በመደወል በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲያገኝ በመደረግ ላይም ነው፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ቋንቋዎች በክልሎች መረጃ የሚሰጡ የጥሪ ማዕከላት 6599 ለደቡብ ክልል፣ 6244 ለትግራይ ክልል፣ 6955 ለኦሮሚያ ክልል፣6407 ለድሬደዋ፣ 6982 ለአማራ ክልል ተዘጋጅተዋል ፡፡
የግብረሀይሉ ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የትምህርት እንቅስቃሴውን ከመደገፍ አንጻር ዩንቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቻው በየክፍሎቻቸው ሆነው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ተጠቅመው ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
ሰብሳቢው የክፍያ ስርዓትን በተመለከተ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከሚሰጡ ትምህርቶች በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክፍያ መፈጸም በሚቻልባቸው አሰራሮች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመተግበር አማራጮች እንዲቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የቴክኖሎጂ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ፣ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ያካተተ መሆኑን ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡