በም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በጄኔቫ በሚካሄደው የስደተኞች ፎረም በመካፈል ላይ ነው
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ዛሬ በተጀመረው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ፎረም በመካፈል ላይ ይገኛል።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ፎረም ኢትዮጵያ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ፓኪስታንና ኮስታሪካ መድረኩን በተባባሪነት እየመሩት መሆኑ ታውቋል።
የዓለም ሀገራት መሪዎች እና ድርጅቶች የሚሳተፉበት ይህ ጉባኤ በስደተኛ ተቀባይ ሀገራት ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፣ ስደተኞችን መልሶ ማቋቋም፣ ስደተኞች ወደ 3ኛ ሀገር የሚዛወሩበትን ዕድል ማስፋት እና ዜጎች ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ አስቀድሞ መከላከል በሚሉት አጀንዳዎች ላይ ይመክራል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ በርካታ የጎረቤትና ሌሎች ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በሀገሪቱ የተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲለውጡ ማስቻሏን ገልጿል።
ሀገሪቱ ስደተኞች የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያደረገችበት የፖሊሲ ማሻሻያ ለሌሎች ስደተኛ ተቀባይ ሀገራት አርአያ ሊሆን እንደሚገባውም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ምንጭ፡-ኢቢሲ