የእስራኤል እና ሱዳን የኡጋንዳ ውይይት አንደምታው ምን ይሆን?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከሰሞኑ በአፍሪካ ያደረጉት ጉብኝት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከአሜሪካ ጉብኝታቸው መልስ ወደ ኡጋንዳ አምርተው ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በኢንቴቤ ባደረጉት ውይይትም ከእስራኤል ወደ ኡጋንዳ የቀጥታ በረራ እንዲኖር ለማድረግ የተነጋገሩ ሲሆን ይህም የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ኡጋንዳ ኤምባሲዋን ከቴልአቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንድታዛውርም ከእስራኤል በኩል ጥያቄ መቅረቡም ተሰምቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በኡጋንዳ ጉብኝታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ጋር መወያየታቸውም የተሰማ ሲሆን ይህ ደግሞ መካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ በበርካታ ሃገራት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከአልቡርሃን ጋር በነበራቸው ውይይት እስራኤል ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ብሎም ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደምትፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በኢንቴቤ የተደረገውን ውይይት ያዘጋጁት ደግሞ የኡጋንዳው ፕሬዚዳት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ሃገራት በመካከላቸው ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች ዙሪያ በትብብር እና በቅንጀት ለመስራትም ንግግር አድርገዋል ነው የተባለው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ሱዳን በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ያለው ለውጥ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሻግራት እምነታቸው መሆኑንም መግለጻቸውን ጽ/ቤታቸው ይፋ አድርጓል፡፡
ይሁንና ይህ የእስራኤልና የሱዳን ውይይት በተወሰኑ የሱዳን ሰዎች ብቻ እንደሚታወቅ ነው የተገለጸው፡፡
የሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ ፈይሰል ሳሊህ፣ ፕሬዚዳንት አልቡርሃን በኡጋንዳ ስለሚያደርጉት ጉብኝትም ሆነ ከእስራኤል ጋር ስለተደረገው ውይይት መረጃ እንደሌላቸው ነው ያስታወቁት።
የሱዳን ካቢኔም ቢሆን በጉዳዩ ዙሪያ አለመምከሩን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ከኡጋንዳ ጉብኝት ሲመለሱ ዝርዝር ማብረራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት አልቡርሃን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር ያደረጉት ውይይት የፍልስጤም ባለስልጣናትን ማስቆጣቱ እየተዘገበ ሲሆን ባለስለጣናቱ የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን ውይይት ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚደረግ የፖለቲካ ሴራ ሲሉ ኮንነውታል።
ሱዳንን ጨምሮ የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት በቅርቡ የእስራኤልና ፍልስጤምን ግጭት ብሎም የቀጣናውን ሰላም በዘላቂነት መፍታት ያስቻላል የተባለውንና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን የሰላም እቅድ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዓረብ ሊግ 22 ሀገራት ሱዳንን ጨምሮ 19ኙ እስካሁን እንደ ሀገር ለእስራኤል እውቅና አልሰጡም፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ