በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት በመላው ጣሊያን የእንቅስቃሴ እገዳ ታወጀ
በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት በመላው ጣሊያን የእንቅስቃሴ እገዳ ታወጀ
ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ከቀናት በፊት ሰሜናዊ ክፍሏን ከእንቅስቃሴ ውጭ ያደረገችው ጣሊያን ከዛሬ መጋቢት 01 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመላ ሀገሪቱን እንቅስቃሴ ገድባለች፡፡
ቫይረሱ ክፉኛ ያጠቃው ሰሜናዊው የጣሊያን ክፍል አደገኛ ቀጣና ተብሎ ቢለይም አሁን ላይ ግን መላው የሀገሪቱ ግዛቶች ከፍተኛ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ሁነቶች ሁሉ እንዳይከናወኑ መታገዳቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት፣ በተለይም በሀገራቀፍ ደረጃ፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተናገዱን ተከትሎ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫውን የሰጡት፡፡ በመንግስት የተወሰደው መላ ሀገሪቱን በስጋት ቀጣናነት ያካተተ እርምጃም፣ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተወሰነ ነው ብለዋል፡፡
በሰሜን ጣሊያን መንግስት የእንቅስቃሴ እገዳ ማወጁን ተከትሎ የሚላን ነዋሪዎች በአንድ ሱተርማርኬት ሲሸምቱ
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከቻይና ውጭ የተወሰደ የመጀመሪያው ጠንካራ እርምጃ በተባለው በዚህ የጣሊያን መንግስት ውሳኔ፣ መላ ሀገሪቱ የሰሜን ጣሊያን እጣ ፋንታ ደርሶታል፡፡ ይሄም ማለት ከ60 ሚሊዮን በላይ የጣሊያን ህዝብ እንዳሻው መንቀሳቀስ አይችልም ማለት ነው፡፡
ከስጋቱ ጋር በተያያዘ በጣሊያን ሁሉም ስፖርቶች ቢያንስ እስከ መጋቢት 25 እንዲቋረጡ መወሰኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ይፋ አድርገዋል፡፡
እገዳው የሀገሪቱ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኖች የሚያደርጉትን ዓለማቀፍ ውድድሮች አያካትትም፡፡
በዓለም ዙሪያ እስካሁን ከ113,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ከ 4,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ከነዚህም 9,172 የቫይረሱ ተጠቂዎች ከጣልያን ሲሆኑ በሀገሪቱ 463 ሞት ተመዝግቧል፡፡
በኤሲያ (በቻይናና ደቡብ ኮሪያ) አዲስ የሚመዘገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በአውሮፓና በአሜሪካ ግን ቁጥሩ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡