የሞሮኮው ንጉስ የአቡዳቢውን ልዑል መሃመድ ቢን ዛይድን አመሰገኑ
መሪዎቹ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በተመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮችም ላይ በስልክ ተወያተዋል
ልዑል አልጋወራሹ አሜሪካ ሞሮኮ በምዕራባዊ ሰሃራ ላይ ላላት ሉዓላዊነት እውቅና መስጠቷን እና ሞሮኮ ከእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመሯን ተቀብለዋል
የሞሮኮው ንጉስ መሃመድ 6ኛ የአቡዳቢውን ልዑል አልጋወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል የበላይ አዛዥ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን አመሰገኑ፡፡
ንጉስ መሃመድ ልዑሉን ያመሰገኑት ለሞሮኮ ባሳዩት እና በሰጡት ድጋፍ ነው፡፡
በስልክ በነበራቸው ቆይታ የሃገራቱን ወንድማዊ ግንኙነት ያነሱት መሪዎቹ ግንኙነቱ ይበልጥ ተጠናክሮ የህዝባቸውን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ ስለሚችልበት ሁኔታ ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በተመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮችም ላይ ተወያተዋል ፡፡
ልዑል አልጋወራሹ አሜሪካ ሞሮኮ በምዕራባዊ ሰሃራ ላይ ላላት ሉዓላዊነት እውቅና መስጠቷን እና የሞሮኮ መንግስት ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማድረግ መወሰኑን ተቀብለዋል፡፡
እርምጃው ለቀጣናው መረጋጋት፣ ብልጽግና እና ሰላም የጋራ ጥረቶች ማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው ልዑል አልጋወራሹ አስረግጠው የተናገሩት፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ሃሙስ ምሽት በእስራኤል እና በሞሮኮ መካከል ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ከሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱ ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ትልቅ ስኬት መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው ያስታወቁት፡፡
ሞሮኮ እ.ኤ.አ በ1777 ለአሜሪካ እውቅና መስጠቷን በማስታወስም ሞሮኮ በምዕራባዊ ሰሃራ ላይ ላላት ሉዓላዊነት እውቅና መስጠቱ ተገቢ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡፡