ቁጥሩን ለማመጣጠን ያስችላል በሚል የውጭ ሃገራት ዜጎች ቁጥርን የሚገድብ አዲስ ረቂቅ ህግ አዘጋጅታለች
ኩዌት በራሷ እና በውጭ ሃገራት ዜጎች መካከል ያለውን የቁጥር ልዩነት ለማመጣጠን የሚያስችል ረቂቅ ህግ አዘጋጀች
በሃገሯ የሚኖሩ ውጭ ሃገራት ዜጎች ቁጥር ከራሷ ዜጎች ቁጥር መብለጥ ያሳሰባት ኩዌት አዲስ የስነ ህዝብ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቷ ተሰምቷል፡፡
ረቂቅ ህጉ የቁጥር ልዩነቱን ለማመጣጠን እና በሃገሪቱ የሚኖሩ የየትኛውም ሃገራት ዜጎች ቁጥር ከራሷ ዜጎች ቁጥር እንዳይበልጥ የሚያስገድድ ነው፡፡
ህጉ በውጭ ሃገራት ዜጎች የተያዙ የስራ ዘርፎችን ለራሷ ዜጎች ለማመቻቸት በማሰብ ተዘጋጅቷልም ተብሏል፡፡
ይህም ከአጠቃላይ ህዝቧ በቁጥር የማይተናነሱት የውጭ ሃገራት ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እስከማስገደድ የሚደርስ ነው፡፡
በቁጥር ከሃገሪቱ ዜጎች የሚበልጡት ህንዳውያንና ግብጻውያን በረቂቅ ህጉ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
ለሃገሪቱ ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ህግ የሚጸድቅ ከሆነ 844 ሺ ህንዳውያን እና ሩብ ሚሊዬን ያህል ግብጻውያን የስንብቱን ገፈት የሚቀምሱ ይሆናልም ብሏል ተነባቢው የሃገሪቱ ጋዜጣ ’ኻሌጅ ታይምስ‘፡፡
ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ያሳሰባት ኩዌት ለዜጎቿ የስራ እድልን መፍጠር ትፈልጋለች፡፡ ይህ ደግሞ በሃገሯ በሚሰሩ የውጭ ሃገራት ዜጎች የተያዙ የስራ ዘርፎችን ነጻ በማድረግ የሚሆን ነው፡፡
አል-ራይ የተሰኘው ሌላኛው የሃገሪቱ ጋዜጣ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የውጭ ሃገራት ዜጎች መብዛት ለከፋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እና የተጠቂዎች ቁጥር ያጋልጠናል የሚል የመከራከሪያ ሃሳብን እንደሚያቀርቡም ይጠቅሳል፡፡
ከሌሎች ሃገራት ዜጎች የሚቀርቡ ስራ ማመልከቻዎች ውድቅ እንዲደረጉ፣ በሂደት ላይ ያሉ ካሉ እንዲሰረዙ ለማድረግ የሚቀርቡ ጥያቄዎችም አሉ፡፡
የተባለውን ጥሶ የተገኘ ከአስር ዓመታት ባልበለጠ እስራት እና ከ100 ሺ ዲናር (10 ነጥብ 5 ሚሊዬን ብር ገደማ) ባልበለጠ ወይም ከሁለቱ በአንዱ እንዲቀጣ ረቂቅ ህጉ ያስቀምጣል፡፡
የሃገሪቱ ባለስልጣናነትም ሃሳቡን ተቀብለውታል ተብሏል፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በኩዌታውያን ይያዛሉ በመባሉም ተደስተዋል እንደ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ፡፡ ከሃገሪቱ መንግስት ተቀጣሪዎች 26 በመቶ ያህሉን የያዙት የውጭ ሃገራት ዜጎች ናቸው፡፡
ኩዌት ይህ ለምን አሳሰባት?
ኩዌት በውጭ ሃገራት ዜጎች የመጥለቅለቋ ጉዳይ እንዳሳሰባት ስትገልጽ ዛሬ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንደምትፈልግ ከመግለጽም አልፋ መተግበር ከጀመረችም ዋል አደር ብላለች፡፡ ይህ ታዲያ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሯ እና ከውጭ ሃገራት ዜጎች የቁጥር ምጣኔ የሚመነጭ ነው፡፡
የኩዌት የመረጃ ሚኒስቴር የባለፈው ዓመት መረጃ እንደሚያመለክተው የሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር 4 ነጥብ 7 ሚሊዬን ደርሷል፡፡
ከዚህ ቁጥር ውስጥ 30 በመቶ ያህሉ የሃገሪቱ ዜጎች ሲሆኑ 70 በመቶው ደግሞ የውጭ ሃገራት ዜጎች ናቸው፡፡
ይህም ነው የሃገሪቱን ባለስልጣናት እጅግ የሚያሳስበው፡፡
በዜጎች ቁጥር ብልጫ መኖሩ ለሃገራችን ቀጣይ እጣ ፋንታ ፈታኝ ይሆናል በሚልም ብዙዎች ፖለቲከኞች ዓይነተ ብዙ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ከሃገር እንዲባረሩ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ እንዳይሰጣቸው የተሰጣቸውም እንዲሰረዝም አበክረው ይጠይቃሉ፡፡
በተጨባጭ ምን ያህል የውጭ ሃገራት ዜጎች በኩዌት ይኖራሉ?
ዎርልዶ ሜትር የተሰኘው ዓለም አቀፍ የመረጃዎች ድረገጽ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የሃገሪቱን ህዝብ ቁጥር ዝቅ ያደርገዋል፡፡
ወቅታዊ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረባት እስከዛሬዋ ቀን ማለትም አርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ/ም ድረስ አጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር 4.2 ሚሊዬን መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
ይህም 7 ነጥብ 7 ቢሊዬን እንደደረሰ ከሚነገርለት የዓለም ህዝብ ቁጥር የ0 ነጥብ 04 በመቶ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ከዓለም የህዝብ ቁጥር የደረጃ ሰንጠረዥም በ129ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ ያደረጉ ወቅታዊ ስነ ህዝብ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በመረጃው መሰረት ከዚህ አጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር ውስጥ ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ወይም 70 በመቶ ያህሉን የሚሸፍኑት የውጭ ሃገራት ዜጎች ናቸው፡፡ የኤሽያ እና የአረብ ሃገራት ዜጎች አብላጫውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
1 ነጥብ 4 ሚሊዬን ኤሽያውያን፤ 1 ነጥብ 1ሚሊዬን ገደማ የአረብ ሃገራት ዜጎች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡ ከኤሽያውያኑም መካከል አብዛኛዎቹ አብዛኛዎቹ ህንዳውያን ናቸው፡፡ ከ647 ሺ በላይ ህንዳውያንም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በኩዌት የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ከ18 ሺ እንደሚበልጡ የሃገር ውስጥ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዎርልዶ ሜትር ደግሞ ቁጥሩን 74 ሺ ያደርሰዋል፡፡
ኢትዮጵያውኑ በኩዌት ያላቸውን የስራና የኑሮ ሁኔታ ለማስተካከል ከአሁን ቀደም ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮች ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል፡፡