ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ገልጿል
የአውሮፓ ሊጎች በዝግ ሊካሄዱ ነው
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን የሊግ ውድድሮች በዝግ እንዲካሄዱ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ውድድሮቹ ከወርሃ መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በአውሮፓ ብቻ የአንድ መቶ ሺ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ክለቦችን ለከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ የሚዳርግ ነው፡፡
በመሆኑም የእግር ኳስ ቤተሰቡን ጤንነት በጠበቀ መልኩ ወደተለመደው እግርኳሳዊ ሁኔታ ለመመለስና ክለቦችን ከቀውሱ ለመታደግ ጨዋታዎችን በዝግ ስቴዲየምም ቢሆን መጀመርና የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቅ እንደሚበጅ ከጣሊያኑ ጋዜጣ ዴሎ ኮሪዬር ጋር ቆይታ ያደረጉት ሴፈሪን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ እየተዘጋጀን ነው ያሉም ሲሆን የየሃገራቱ ሊግ የሚጀመር ከሆነ የሻምፒዮንስ እና የአውሮፓ ሊግ ጨዋታዎችን ጎን ለጎን ማካሄዱ እንደማይከብድ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ይህ ስምምነትን የሚፈልግ ነው የውድድር ዓመቱን መራዘም እንደማይደግፉት ስሎቬኒያዊው ሴፈሪን ገለጻ፡፡
እስከ መጪዎቹ የመስከረምና ጥቅምት ወራት መራዘሙ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ላይ ጫናን ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ እንደሌለውም ይናገራሉ፡፡
“የጀመርነውን መጨረስ እንችላለን ግን ውሳኔዎችን ማክበር የግድ ይለናል”ም ይላሉ፡፡
ለደጋፊዎች፣ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ጤና ነው ቅድሚያ እንደሚሰጡም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡