በፍንዳታ የወደመውን የቤሩትን አካባቢ ስንት ቢሊዬን ዶላር መልሶ ይገነባዋል?
የሃገሪቱ የወጪ እና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ምናልባትም እስከ ቀጣዮቹ 8 ወራት ሊቆም ይችላል
አካባቢውን መልሶ ለመገንባት እስከ 15 ቢሊዬን ዶላር ሊያስፈልግ ይችላል ተብሏል
በቤሩቱ ፍንዳታ የወደመውን አካባቢ መልሶ ለመገንባት እስከ 15 ቢሊዬን ዶላር ያስፈልጋል
በከትናንት በስቲያው የቤሩት ወደብ ፍንዳታ የወደመውን አካባቢ መልሶ ለመገንባት ሊባኖስ ምናልባትም እስከ 15 ቢሊዬን ዶላር ሊያስፈልግ እንደሚችል አንድ ከፍተኛ የሃገሪቱ መንግስት አማካሪ ተናገሩ፡፡
የፕሬዝዳንት ሚሼል አውን የምጣኔሃብት ጉዳዮች አማካሪ ናቸው የተባለላቸው ሻርቤል ካርዳሂ ካሳን ጨምሮ የፈራረሱትን መልሶ ለመገንባት እስከ 15 ቢሊዬን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ሊያስፈልግ ይችላል ብለዋል፡፡
70 በመቶ ያህሉ የሃገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ በቤሩት ወደብ የሚፈጸም ነው አማካሪውን ዋቢ እንዳደረገው እንደ አረብ ኒውስ ዘገባ ከሆነ፡፡
“ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚደርሰው ቀሪው የንግድ ልውውጥ ደግሞ በሃገሪቱ አየር መንገድ እና በሌሎች ወደቦች በኩል የሚፈጸም ነው፡፡ ከሶሪያ ጋር የምንዋሰንበት ድንበር ቢከፈት እንኳን እስከ 20 በመቶ ድረስ ብቻ ነው ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት የሚችለው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የ5 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸው የገቢ ምርቶች ገቢ ማድረግ እንዲሁም የ2 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸው የወጪ ምርቶችን መላክ ለቀጣዮቹ ስምንት ወራት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የ4 ቢሊዬን ዶላር ኪሳራ ወይም ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት የ15 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡” ሲሉም ያስቀምጣሉ፡፡
ሊባኖስ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ውጭ ልታንሰራራ የምትችልበት አቅም እንደሌላትም ገልጸዋል፡፡
የከተማይቱን ወደብ እና አካባቢውን ባወደመው ፍንዳታ ከ3 እስከ 5 ቢሊዬን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያለው የንብረት ውድመት መድረሱን ዓለም አቀፍ የድጋፍ ጥሪ ያቀረበው የሃገሪቱ መንግስት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ንዝረቱ እስከ ቆጵሮስ ተሰምቷል የተባለለት ፍንዳታው የከፋ ነው በተባለ ምጣኔሃብታዊ ድቀት ውስጥ ለምትገኘው ሊባኖስ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡
ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎቿን ስቃይ የሚበረታ አጋጣሚም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከአጠቃላይ ህዝቧ ግማሽ ያህሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ከ135 የሚልቁ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው ፍንዳታ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጎድተዋል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ቤት አልባ ሆነዋል፡፡
ፍንዳታው በወደቡ ይገኝ በነበረ አንድ መጋዘን ለ7 ዓመታት ተከማችቶ በነበረ አሞኒዬም ናይትሬት ምክንያት የተፈጠረ ነው መባሉም የሚታወስ ነው፡፡