በቅርቡ ከሳዑዲ የገባ ሰው በቫይረሱ መያዙ ተነግሯል
ሌሶቶ ኮሮና የተገኘባት የመጨረሻዋ አፍሪካዊት ሃገር ሆነች
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሃገር ሌሶቶ የመጀመሪያውን የኮሮና ታማሚ ማግኘቷን አስታውቃለች፡፡ የቫይረሱን መገኘት ሪፖርት ያደረገች የመጨረሻዋ አፍሪካዊት ሃገር ሆናለች፡፡
አሁን ላይ 54ቱም የአህጉሪቱ ሃገራት ቫይረሱን ሪፖርት አድርገዋል፡፡
በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል የተባለለት ሰው በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሌሶቶ የገባና የውጭ ጉዞ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ሰውዬው በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው ለ597 ተጠርጣሪዎች በተደረገ ምርመራ ነው፡፡
ታማሚው በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ እና ሳዑዲ ከገቡ 81 መንገደኞች መካከልም አንዱ ነው እንደ ደቡብ አፍሪካው ‘አይ ዊትነስ ኒውስ’ ዘገባ፡፡
በአሁኑ ሰዓት ተለይቶ እንዲቆይ ተደርጓልም ብሏል የሃገሪቱን ጤና ሚኒስቴር ዋቢ ያደረገው አሶሼትድ ፕሬስ፡፡
የሁለት ሚሊዬን ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ሌሶቶ 11 ሺ 350 ዜጎቿ በቫይረሱ በተያዙባት ደቡብ አፍሪካ ዙሪያዋን የተከበበች ናት፡፡
ቫይረሱን ለመመርመር የሚያስችል አቅም የሌላት መሆኑን ተከትሎ ናሙናዎችን ወደ ጎረቤት ሃገር ደቡብ አፍሪካ ልካ ነው የምታስመረምረው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ከ71 ሺ 200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና 2 ሺ 411 ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡