አመታትን ያስቆጠረው የሊቢያ የእርስበርስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው
ከኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ መንግስት ውድቀት እና ከእሳቸው ህልፈት በኋላ ሊቢያ ላለፉት ዘጠኝ አመታት እንደታመሰች ዛሬም ቀጥላለች፡፡
አሁን ላይ የሊቢያ መንግስት ለ ሁለት ተከፍሎ በፍልሚያ ላይ የሚገኝ ሲሆን ማዕከሉን ቤንጋዚ ላይ ያደረገውን መንግስት ጦር መቋቋም የተሳነው በተባበሩት በንግስታት እውቅና ያለው የትሪፖሊው ሌላኛው መንግስት ከቱርክ የጦር ሰራዊት እና የሎጅስቲክስ ድጋፍ ሊቀርብለት ተስማምቷል፡፡
በኮማንደር ካሊፋ ሃፍታር የሚመራው የቤንጋዚው መንግስት ጦር ጫናውን አበርትቶ ወደትሪፖሊ የሚያደርገውን ጉዞ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የቱርክን ጦር የትሪፖሊውን መንግስት ለመደገፍ ወደ ሀገሪቱ እንደሚገባ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የቱርክን ጦር ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ካለውና መቀመጫውን ትሪፖሊ ካደረገው የአል ሳራጅ ጦር ጋር መዋጋት መቀጠሉን መቀመጫውን ቤንጋዚ ያደረገው የጄነራል ከሊፋ ሃፍታር ጦር አስታውቋል፡፡
በቅርቡ ወደ ሊቢያ እንደሚገባ ለሚጠበቀው የቱርክ ጦር ሚስራታና ዙዋራን ጨምሮ በ5 የወደብ አካባቢዎች አቀባበል ሊደረግ ታስቧል ያሉት የቤንጋዚው ጦር ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል አህመድ አል ሚስማሪ፣ ሚስራታ፣ ትሪፖሊ እና ዙዋራ ከተሞች በማዕከልነት እንዲያገለግሉ በማሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአል ሳራጅን ጦር አሸባሪ ያሉት ቃል አቀባዩ የማይተካ አየር ማረፊያንና የትሪፖሊ ወደብን የቱርክ ጦር ቤዝ ለማድረግ መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡
ትናንት ሃሙስ ሚስራታ፣ዝሊተንና አል ኩምስ ከተሞች ላይ የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውን የገለጹም ሲሆን በአሸባሪዎቹ የጦር መሳሪያ ይዞታ ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
አል ሚስማሪ አያይዘውም በድብደባው የቱርክ ዜግነት ያላቸው የአሸበሪው ሚሊሻ ታጣቂዎች ደጋፊዎች ተገድለዋል ያሉም ሲሆን የጦሩ እግረኛ ወታደሮች ወደ ትሪፖሊ እየተጠጉ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ በትሪፖሊው የአሸባሪ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል እንዳለም ነው ቃል አቀባዩ ዛሬ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የተናገሩት፡፡