የሞንጎሊያ ፕሬዝዳንት ከቻይና ጉብኝት መልስ ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ
የሞንጎሊያ ፕሬዝዳንት ከቻይና ጉብኝት መልስ ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ
የሞንጎሊያ ፕሬዝዳንት ባቱልጋ ካልትማ እና ሌሎች አብረዋቸው ትናንት በቻይና የአንድ ቀን ቆይታ ያደረጉ ባለስልጣናት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለ14 ቀናት ክትትል ሊደረግላቸው ለይቶ ማቆያ ገብተዋል፡፡
በቻይና ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል ሽርጉድ ውስጥ እያለች በሀገሪቱ ጉብኝት በማድረግ ባቱልጋ የመጀመሪያው ሀገረ መሪ ናቸው፡፡
መሪው ከቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቂያንግ ጋር ቫይረሱን በጋራ መከላከል በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡
“በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሞንጎሊያው ፕሬዝዳንት ባቱልጋ ካልትማ ወደ ሀገራችን ጉብኝት ማድረጋቸው፣ የእርስ በርስ የመተባበር መንፈሳችንን የሚያንጸባርቅ ነው” ሲሉ ዢንፒንግ ጉብኝቱን አሞካሽተዋል፡፡
ሞንጎሊያ ለቻይና 30,000 በጎችን በስጦታ መልክ እንደምትለግስም ፕሬዝዳንት ባቱልጋ ቃል ገብተዋል፡፡ ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረትም ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ ቫይረሱን እንደምትቆጣጠረው እምነት እንዳላቸው እና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ሞንጎሊያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዢንፒንግ ለሀገራቱ ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ቫይረሱን ለመቆጣጠርም ቻይና ከመላው ዓለም ጋር ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
የሞንጎሊያው ፕሬዝዳንት እና የቻይና ልኡካቸው አባላት ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን እስኪያረጋግጡ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ ዉስጥ መግባታቸውን የሀገሪቱን ሚዲያ ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቻይና ሰሜናዊ ጎረቤት የሆነችው ሞንጎሊያ፣ ቫይረሱ እስካሁን ወደ ሀገሪቱ ባይደርስም ለጥንቃቄ በሚል ት/ቤቶችን ከዘጋች ቆይታለች፡፡ ት/ቤቶቹ ከዚህም በኋላ ከአንድ ወር በላይ ተዘግተው እንደሚቆዩ ይጠበቃል፡፡