ባለፈው ሀሙስ 89 ወታደቿ የተገደሉባት ኒጀር የ 3 ቀን ብሔራዊ ሀዘን አወጀች፡፡
የሀዘን ቀኑ የታወጀው ባለፈው ሀሙስ ለተገደሉ 89 የሀገሪቱ ወታደሮች ነው፡፡ ወታደሮቹ ባለፈው ሀሙስ ከፍተኛ መሳሪያ በያዙ ታጣቂዎች በማሊ ድንበር አቅራቢያ ምዕራብ ኒጀር በሚገኝ የጦር ሰፈር ውስጥ ነው የተገደሉት፡፡
በዚህ ምክኒያት የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል አህመድ ሞሀመድ ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡ ጄነራል ሞሀመድ ጦሩን በመሩበት ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ውስጥ የአል-ቃኢዳ እና አይኤስ ጥቃት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል ነው የተባለው፡፡
ሜጀር ጄነራል ሳሊፉ ሞዲ በጄነራል ሞሀመድ ቦታ የሀገሪቱ ጦር መሪ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ጦር በወሰደው የመልሶ ማጥቃ እርምጃ 77 አሸባዎችን ገድያለሁ ብሏል፡፡
ትናንት ጥር 04/2012 ዓ.ም በታወጀው የሶስት ቀን የሀዘን ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማዋ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል፡፡
ፕሬዝዳንት ሞሀመዱ ኢሱፉ በወታደሮቹ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በገለጹበት መልዕክት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ ከወር በፊት በሀገሪቱ አንድ የጦር ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 71 ወታደሮች ተገድለዋል፡፡
የኒጀር እና ማሊ ጦር በቀጣናው የጂሀዲስቶችን ሰርጎ-ገብ እንቅስቃሴ ለመከላከል በጋራ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ሲኤንኤን፣ ይሄም ወታደሮችን ለጥቃት ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሁለት የፈረንሳይ ሄሊኮፕተሮች ማሊ ላይ ተከስክሰው 13 የፈረንሳይ ወታደሮች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ በዚሁ ወር ከ50 በላይ የማሊ ወታደሮችም ካምፕ ውስጥ እንዳሉ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ጥቃት ተገድለዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን