ናይጄሪያውያን ሃኪሞች ተጣብቀው የተወለዱ ጨቅላዎችን አለያዩ
ሃኪሞቹ ጋድነስ እና ሜርሲ የተሰኙትንና ተጣብቀው ከተወለዱ 1 አመት ያስቆጠሩትን ጨቅላዎች ለማለያየት የተሳካ ቀዶ ጥገና ማድረጋቸውን ቢቢሲ በአፍሪካ ገጹ አስነብቧል፡፡
በደረትና በሆዳቸው የተጣበቁትን ጨቅላዎች የማላቀቁ ስራ ውስብስብ እና ቀላል እንዳልነበር የተናገሩት የቀዶ ጥገና ሃኪሞቹ ቡድን መሪ ኢማኑዔል አሜህ ወርሃ ህዳር ላይ በተካሄደው ኦፕሬሽን ጨቅላዎቹን ለማላቀቅና በሙሉ ጤንነት ላይ ሆነው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
55 ሺ የአሜሪካ ዶላር ወጪ በጠየቀውና 12 ሰዓታትን በወሰደው ኦፕሬሽን 78 ዶክተሮች መሳተፋቸውንም ነው ቡድን መሪው የተናገሩት፡፡
ሆኖም የጨቅላዎቹ ቤተሰቦች ወጪውን ለመሸፈን የሚችል አቅም የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ በኦፕሬሽኑ የተሳተፉ የአቡጃ ናሽናል ሆስፒታል ሙያተኞች አንዳችም ክፍያ አልተቀበሉም፡፡
የጨቅላ ህጻናቱ ወላጆች ሚካኤል ኤዴህ እና ማሪያ ኦንያ ማርቲንስ ከአመት በፊት ነበር ተጣብቀው የተወለዱትን ልጆቻቸውን በሃገሪቱ ርዕሰ መዲና ወደሚገኘው ሆስፒታል የወሰዱት፡፡
ሆኖም ህጻናቱ መለያየት በሚያስችል ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውን በወቅቱ ገልጸው የነበሩት ሃኪሞቹ ከ15 ወራት ቆይታ በኋላ ቀዶ ጥገናውን በተሳካ ሁኔታ አካሂደዋል፡፡
በአቡጃ ናሽናል ሆስፒታል በባለፉት 20 ዓመታት 11 ቀዶ ጥገናዎች በተሳካ ሁኔታ ተካሂደዋል፡፡ ነገር ግን ቀዶ ጥገናዎቹ በዋናነት በሆዳቸው ተጣብቀው በተወለዱ መንትያዎች ላይ የተካሄዱ ነበሩ፡፡
በደረት አካባቢ ለተጣበቁ መንትያዎች ቀዶ ጥገና ሲደረግ የመጀመሪያው ስለመሆኑም ነው የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ጃፍ ሞሞህ የተናገሩት፡፡
ጋድነስ እና ሜርሲ በተወለዱበት ጊዜ እጅግ አዝነው እንደነበር የገለጹት የጨቅላዎቹ ወላጆች በልጆቻቸው ጤንነት እና በኦፕሬሽኑ ስኬታማነት ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ሃኪሞቹንና ሆስፒታሉን ስለ ቀናዒ ትብብራቸው አመስግነዋል፡፡
የሃገሪቱ ጤና ሚኒስትርም የሃኪሞቹን ጥረት ለመደገፍና ለማድነቅ የጨቅላዎቹን ቤተሰቦች ለማግኘትም በሆስፒታሉ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የሃገሪቱ ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴርም ለጨቅላዎቹ እናት ስራ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ