ኖርዌይ ከሊቢያ ወጥተው በሩዋንዳ የተጠለሉ 600 ስደተኞችን ልትወስድ ነው
ስካንዲኒቪያዊቷ ሃገር ከሊቢያ እስር ቤቶች ወጥተው በሩዋንዳ የተጠለሉ 600 ስደተኞችን በዚህ ዓመት ልትወስድ ስለመሆኑ አስታውቃለች፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ኖርዌይ ይህን የምታደርገው በሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ የሚፈጸመውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማዳከም በማሰብ ነው፡፡
ስዊድን በባለፈው ወር 7 ስደተኞችን ስለመውሰዷ የገለጹት የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሰንት ቢሩታ ኖርዌይ 5 መቶ ስደተኞችን ለመውሰድ መስማማቷን ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ የኖርዌይ ፍትህ ሚኒስትር ጆራን ካልማየር አረጋገጡልኝ እንዳለው ከሆነ ደግሞ ሃገራቸው 6 መቶ ስደተኞችን በዚህ ዓመት ከሩዋንዳ ትቀበላለች፡፡ የምትቀበለው የስደተኞች ቁጥር ግን ባለፈው ዓመት ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት ከ3 ሺ እንደማይበልጥም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በ1994ቱ የእርስ በርስ ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎቿን ያጣችው ሩዋንዳ ሜዲትራኒያንን በማቋረጥ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ተይዘው በሊቢያ የሚታሰሩ አፍሪካዊ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ተስማምታለች፡፡
ምንጭ፡-ሮይተርስ