በ2019 የኢትዮጵያና የዓለም የመዝናኛ ኢንዱስትሪ በርካታ ስመጥር ጠቢባንን አጥቷል
2019ን ያልተሻገሩ አርቲስቶች
የተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2019 ዓ.ም. በመዝናኛው አለም ኢንዱስትሪ የተለያዩ አስደሳችም አሳዛኝም በርካታ ክስተቶችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ በዚሁ አመት በርካታ ስመጥር አርቲስቶች በትዳር ሲተሳሰሩና ለፍሬ ሲበቁ አለምን እስከወዲያኛው የተሰናበቱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ከልጅ እስከ አዛውንት የጥበብ አድናቂዉን ቤተሰብ በስራዎቻቸው ያስደመሙ በርካታ አርቲስቶች 2019ን መሻገር ተስኗቸው ለአይቀሬው ሞት እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡እኛም በዚህ ጽሁፍ ዳግም ላይመለሱ ካሸለቡ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አርቲስቶች መካከል ለትውስታ ያክል ጥቂቱን በአጭሩ እንቃኛለን፡፡
በ2019 ያጣናቸው ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች
ኤሊያስ መልካ
የኢትዮጵያ የጥበብ ዓለም ካጣቸው ብርቅዬ ጠቢባን መካከል በ42 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት የሆነው ኤልያስ መልካ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ማለዳ ነው።
ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል ሲሆን የሚኪያ በኃይሉ ፣የእዮብ መኮንንን ፣የጎሳዬ ተስፋዬ፣ የኃይሌ ሩት፣ የአረጋኽኝ ወራሽ፣ የኩኩ ሰብስቤ፣ የትዕግስት በቀለ፣ የትግርኛ ዘፋኝዋ ማህሌት ገብረ ጊዮርጊስ እና የጌቴ አንለይ የሙዚቃ ሥራዎች የኤሊያስ አሻራ ካረፈባቸው ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያው ኤሊያስ መልካ ትዳር ያልመሰረተ ሲሆን፣ በተለያዩ ሥራዎቹ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል።
ኤልያስ መልካ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በፋና የድምፃውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ኤሊያስ በመዲና፣ ዜማ ላስታስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ውስጥ ተጫውቷል።
ተዘራ ለማ
በበርካታ ፊልሞች ላይ በትወና የሚታወቀው አርቲስት ተዘራ ለማ በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2019 ነው፡፡
አርቲስት ተዘራ ከ20 በላይ ፊልሞች ላይ የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ወክሎ ተጫውቷል፡፡ የበኩር ልጅ፣ ፍቅር ባጋጣሚ፣ ታሰጨርሺኛለሽ፣ ፍቅር በይሉኝታ፣ አልወድሽም፣ ወንድሜ ያዕቆብ፣ ኢንጂነሩ፣ፍፃሜው፣እሷን ብዬ እና ጥቁር እና ነጭ ከተወነባቸው ፊልሞች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
በ“የበኩር ልጅ” ፊልም ላይ ባሳየው ድንቅ የትወና ብቃት በ9ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ “የአመቱ ምርጥ ተዋናይ” ተብሎ ተሸልሟል፡፡ በ”ፍቅር ቃል” ፊልም ላይም እንዲሁ ባሳየው ብቃት ከነ ቤተሰቡ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
አርቲስት ተዘራ በጥበቡ ዓለምከተወዛዋዥነት እና ጊታር ተጨዋችነት እስከ ታዋቂ ተዋናይነት ለመድረስ በቅቷል፡፡ አርቲስቱ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነበር።
ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ
በተለይ በቴያትር እና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ትወና፣ አዘጋጅነት እና አርትኦት የሚታወቀው ሁለገብ አርቲስት ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2019 ካጣቻቸው ድንቅ የጥበብ ሰዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ገመና ቁጥር አንድና ወላፈን የተባሉ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችም ላይ የተወነው ጫንያለው ሙዚቀኛ (ሳክስፎን ተጫዋች)፣ ተዋናይ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ የቴአትር ሙያ አሠልጣኝ፣ አዘጋጅና የቴአትር ጽሑፎችን ገምጋሚ ሆኖ በመሥራት ለሀገሩ ኪነ ጥበብ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ ይታወሳል፡፡
ውጫሌ 17፣ የሌሊት እርግቦች፣ ካሊጉላ እንዲሁም ትዕይንተ ጥበባት ከተወነባቸው ቴአትሮችና ዝግጅቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የቃቄ ውርድወት የተሰኘውንና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈውን ሙዚቃዊ ቴአትር የደረሰውም ጫንያለው ነው፡፡
ታኅሣሥ 29 ቀን 1955 ዓ.ም. የተወለደው አርቲስት ጫንያለው ለፊልም ሥራ ወደ እስራኤል በሄደበት አጋጣሚ በፅኑ በመታመሙ የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ በ57 ዓመቱ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. አርፎ ሥርዓተ ቀብሩም እዚያው እስራኤል ተፈጽሟል፡፡
ታደለ ታምራት
ሌላኛው ሁለገብ የኪነጥበብ ባለሙያ አርቲስት ታደለ ታምራት በ84 ዓመቱ መስከረም 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው ያረፈው፡፡
ከ38 ዓመታት በላይ በብሄራዊ ቴአትር ያገለገለው አርቲስት ታደለ በሙዚቃ ሥራው በዳንስ፣ በውዝዋዜ በቴአትር እንዲሁም በኬሮግራፊና የሙዚቃ ዝግቶችን በማዘጋጀት በኃላፊነት ያገለገለ ሲሆን፣ በሙያውም በርካታ አንቱ የተባሉ ሙያተኞችን አፍርቷል፡፡
ሙያውን ለማሳደግ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዛዋወር የየብሔረሰቡን የሙዚቃ፣ የባህል ውዝዋዜና ዳንኪራ ከእነ አልባሳታቸው በማጥናትና ለሙያተኞች በማስጠናት በአገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ አገሮች የኢትዮጵያን ባህል አስተዋውቋል፡፡ለአብነት ያህልም ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ኮሪያ እንዲሁም አሜሪካና ሜክሲኮ በስራው የተጓዘባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡
አርቲስት ታደለ ታምራት ከባለቤታቸው ወ/ሮ አመለወርቅ ገብረ ኪዳን ዘጠኝ ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ 12 የልጅ ልጆችን እንዲሁም አራት የልጅ ልጅ ልጅንም አይተዋል፡፡
በ2019 ያረፉ የውጭ አርቲስቶች
ከሀገር ውጭ ደግሞ ከካሮል ቻኒንግ ጀምሮ 2019 የበርካታ ዝነኞችን ህይወት ነጥቋል፡፡
በተለይ ሄሎ ዶሊ እና ጄንትል ሜን ፐርፍረ በሎንዲስ በሚለው ተውኔታዊ የሙዚቃ ትእይንቷ የምትታወቀው አሜሪካዊት ድምጻዊ፣ ተዋናይት፣ ዳንሰኛና ኮሜዲያን ካሮል ቻኒንግ በ97 ዓመቷ 2019 ከገባ ከ 2 ሳምንታት በኋላ ጥር 15 በካሊፎርኒያ ህይወቷ አልፏል፡፡
በ1980ዎች እና 90ዎች በአለም ዝነኛ ከነበሩ የአር ኤንድ ቢ ድምጻዊያን መካከል አንዱ የሆነው ጀምስ ኢንግራም ደግሞ በ66 ዓመቱ ጥር 29 ነው የሞተው፡፡
ዳውንፎል በተሰኘው የኦስካር እጩ ፊልም የአዶልፍ ሂትለርን ገጸ-ባህሪ ተላብሶ የተወነው ስዊዘርላንዳዊ ተዋናይ ብሩኖ ጋንዝ በአውሮፓውያኑ የካቲት 16 የምድር ላይ ቆይታውን አጠናቋል፡፡ በ77 ዓመቱ እስከወዲያኛው ያሸለበው ጋንዝ ከ50 ዓመታት በላይ በጀርመንኛ ቲያትር፣ፊልም እና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ የተወነ ሲሆን የጀርመንኛ ተዋኒያን የሚበረከትላቸውን ታላቅ ሽልማት አሸንፏል፡፡
በ2019 አሳዛኝ የሞት ክስተቶች መካከል የግራሚ እጩው ራፐር ኒፕሲ ሀስል ሞት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኒፕሲ መጋቢት 31 በደቡብ ሎስ አንጀለስ ከመልበሻ ቤቱ ውጭ በጥይት ተመትቶ ነው በ33 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው፡፡ የራፐሩ ሞት በወቅቱ የመላው አሜሪካን የመዝናኛ ዓለም ያስደነገጠ ክስተት ነበር፡፡ ትክክለኛ ስሙ ኤርሚያስ አስገዶም የሆነው ኒፕሲ ከኤርትራውያን ወላጆች የተገኘ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ ላይ የነበረ አሜሪካዊ ድምጻዊ ነበር፡፡
የኦስካር አሸናፊው ፕሮዲዩሰር ስቲቭ ጎሊን ደግሞ በ64 ዓመቱ ሚያዝያ 21 በሎስ አንጀለስ አርፏል፡፡ ዘ ሬቨናንት እና ስፖት ላይት ፕሮዱስ ካደረጋቸው ፊልሞች መካከል ናቸው፡፡ ከነዚህም ዘ ሬቨናንት የተሰኘው ፊልም በ2016 በምርጥ ተዋናይ፣ ምርጥ ዳይሬክተር እና ምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፎች ሶስት የኦስካር ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥሞች ደራሲ ጆኒ ክሌግ የካንሰር በሽታ ሀምሌ 16 ለሞት ዳርጎታል፡፡ የግራሚ እጩው እና የቢልቦርድ ሙዚቃ ሽልማት ባለድሉ ጆኒ በ66 ዓመቱ ነው ያረፈው፡፡ ጆኒ ክሌግ የዙሉ ቋንቋን አቀላጥፎ የሚናገር ሲሆን በዚሁ ቋንቋ ባህላዊ ሙዚቃዎችን በተዋበ ድምጹ ለአመታት አቀንቅኗል፡፡
የቶኒ አዋርድን ለ21 ጊዜ በማሸነፍ አቻ ያልተገኘለት የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር እና ዳይሬክተር ሃሮልድ ሃል ፕሪንስ በ91 ዓመቱ ሀምሌ 31 ለሞት እጁን ሰጥቷል፡፡
የቢልቦርድ ሚዩዚክ አዋርድ አሸናፊው ጃራድ አንቶኒ ሂጊንስ፣ በይበልጥ በመድረክ መጠሪያው ጁስ ወርልድ ስያሜው የሚታወቀው አሜሪካዊ ራፐር ቺካጎ አየር ማረፊያ እንዳረፈ በገጠመው ድንገተኛ ህመም በ21 ዓመቱ የተቀጨው በ2019 የመጨረሻ ወር ታህሳስ 8 ነው፡፡
ዓመቱ በተለያዩ በንገዶች ከላይ ከተጠቀሱ ጥቂት ዝነኞች በተጨማሪ በመላው አለም የበርካታ ጠቢባንን ህይወት ነጥቋል፡፡