የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት በቀጣይነት ሴት መሪ እንዲተካኝ እፈልጋለሁ አሉ
በኪጋሊ በተጀመረው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ላይ አገራቸው ሴቶችን ወደ አመራር በማምጣት ስኬታማ መሆኗንም የገለጹት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ሩዋንዳ በዘርፉ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያስከብራት ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ከመቶ በላይ አገሮች ውስጥ በተሠራ ዳሰሳ መሰረት ከመጀመሪያዎቹ አስር አገራት ዝርዝር ውስጥ ገብተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ የመጀመሪያዎቹ አምስት ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ለመግባት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ አገሪቱ ሴቶችን ማብቃት ላይ ለዓመታት ያፈሰሰችው ኃይል ውጤታማ በመሆኑ እንደተደሰቱም ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል። ሴቶች በንግድ፣ በጸጥታ ጥበቃና በፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
2,000 ሰዎች በታደሙት ውይይት ላይ ሴቶች ሁሉም ቦታ እንድትኖሩ እፈልጋለሁ የሰጣችሁኝን የአመራር ቦታ የምትረከበው ሴት እንድትሆን እመኛለሁ ያሉት ፕሬዝዳንት ካጋሜ ንግግሬን የሚያዳምጡ አዳራሹ ውስጥ ያሉ ወንዶች እንደማይቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ የነሱም ምኞት እንደኔ አይነት ሊሆን ይችላልም ብለዋል።
የሩዋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 52 በመቶ የሴቶች ውክልና በመያዝ ግንባር ቀደም ሲሆን ከ26 የካቢኔ መቀመጫ 14ቱ በሴቶች የተያዘ ነው። ሆኖም በፍትሕ እና በንግዱ ዘርፍ አሁንም የወንዶች የበላይነት ይስተዋላል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ