ፖፕ ፍራንሲስ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ቃላቸውን እንዲጠብቁ ተማጸኑ
ፖፕ ፍራንሲስና ሌሎች ሁለት የሀይማኖት መሪዎች ዛሬ ባስተላለፉት ልዩ የገና በዓል መልእክታቸው የደቡብ ሱዳን መሪዎች ቃላቸውን ጠብቀው ቢያንስ የሽግግርና የአንድነት መንግስት በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ እንዲመሰርቱ ጠይቀዋል፡፡
ከሮማን ካቶሊክ ቸርች ፖፕ ፍራንሲስ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ የአንግሊካን ቸርች መሪዎቹ ጀስቲን ዌልባይ እና ጆን ቻልመርስ ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ብዙሀኑ ክርስቲያን የሆነባት የዓለም ወጣቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ሰላም ከሰፈነባት ፖፑ ሊጎበኟት ይችላሉ፡፡ ፖፕ ፍራንሲስ በሚቀጥለው የፈረንጀቹ አዲስ ዓመት ሀገሪቱን “እንደምጎበኝ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ነበር፡፡
የሀይማኖት መሪዎቹ ደቡብ ሱዳን ለእርቅና ለወንድማማችነት እንድትተጋ እንደሚፀልዩ በመልእክታቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና የቀድሞው የአማጺ መሪ ሪክ ማቻር ባለፈው ህዳር ወር የአንድነት መንግስት ለመመስረት የተቀመጠውን ቀነገደብ በ100 ቀናት ማሳለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከተቀመጠውና የመጀመሪያው ከሆነው ስምምነት ቀነገደብ ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ኪርን፣ማቻርንና ሌሎች ፖለቲከኞችን ወደ ቫቲካን በማምጣት መሪዎቹ እንዲጸጸቱና እርቅ እንዲያወርዱ ለማድረግ ጥረው ነበር፡፡
በመጨረሻው የቆይታቸው ቀን ፖፕ ፍራንሲስ ዝቅ በማለት በቀድሞ ተፋላሚዎቹ እግር ላይ ወድቀዉ ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳይመለሱና፣ ባለፈው አመት የደረሱበትን ስምምነት እንዲያከብሩ ሲማፀኑ ተስተውለው ነበር፡፡
ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2011 ነፃ ከወጣች በኋላ ብዙም ሳትቆይ ወደ እርስበርስ ጦርነት መግባቷ የሚታወስ ነው፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ