የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪ በሕይወት ለሌሉት ግለሰብ ኃላፊነት መስጠታቸው እያነጋገረ ነው
ፕሬዚዳንት ሞሃሙዱ ቡሃሪ በናይጄሪያ የኢቦኒ ግዛት ነዋሪ ለነበሩትና አሁን በሕይወት ለሌሉት ግለሰብ ኃላፊነት መስጠታቸው እያነጋገረ ነው፡፡
በፕሬዚዳንቱ ሹመት ያገኙት ግለሰብ መሞታቸውንም የኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ አስታውቋል፡፡ ለሞቱት ግለሰብ የተሰጠው ሥልጣን የፌዴራል ካራክተር ኮሚሽን አባልነት ነው፡፡ ግለሰቡ ኡክውሩ ኃላፊነት የተሰጣቸውና የተመለመሉት በህይወት እያሉ ነው ሲሉ የኢቦኒ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ሹመቱን የሰጧቸው ሰዎች እንዲጸድቁላቸው በጠየቁ ጊዜ ግን ከተሾሙት ውስጥ እኚህ ግለሰብ መሞታቸውን ተገንዝበዋል፡፡ ክፍተቱ የተፈጠረበት ምክንያት ደግሞ የኢቦኒ ባለሥልጣናት አስፈላውን መረጃ ባለመስጠታቸው ነው ተብሏል፡፡ ባለሥልጣናቱም ይህ ስህተት የእነርሱ መሆኑን ገልጸው ለፓርቲው ብሔራዊ የአመራር ኮሚቴ ማሳወቅ እንደነበረባቸው ግለ ሂስ አውርደዋል፡፡
ለፕሬዚዳንት ቡሃሪም ይህንኑ ጉዳይ ማሳወቅ እንደነበረባቸው፣ ለዚህም ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ ነው ያስታወቁት፡፡ የዚህ ስህተት ምክንያትም የሟች ቤተሰቦች የግለሰቡን ህልፈት በይፋ አለመግለጻቸውና መደበኛ የቀብር ሥነ ስርዓት አለማዘጋጀታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ስህተቱ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ አይደለም ሲል ነው የግዛቲቱ አስተዳደር ያስታወቀው፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ የፓርቲው ኃላፊት መሆኑንና መረጃውን መስጠት የነበረበትም ፓርቲው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ህይወቱ ላለፈ ሰው ስልጣን ሲሰጡ የአሁኑ የመጀመሪያ ክስተት አይደለም፡፡ በአውሮፓውያኑ 2017 ከሞቱ ረዥም ጊዜ ለሆናቸው አምስት ያህል ግለሰቦች የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥተዋል ዴይሊ ፖስት እንደዘገበው፡፡