የብልጽግና ፓርቲን ውህደት የተቀበሉ እህትና አጋር ድርጅቶች የፊርማ ሥነሥርዓት ተከናውኗል፡፡
ውህደቱን የተቀበሉት የኢህአዴግ እህት እና አጋር ፓርቲዎች የፊርማ ሥነሥርዓት ህዳር 21ለ2012 በፓርቲዎቹ ሊቀመናብርት ነው የተከናወነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በፊርማው ሥነሥርዓት ወቅት ባደረጉት ንግግር የብልጽግና ፓርቲ /ብልጽግና/ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ወደብልጽግና የሚያሻግር እውነተኛ ድልድይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የብልጽግና መለያ እውነትና እውቀት ነው፤ ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ተስፋ የምትሆን፣ ለመኖር የምታጓጓ እና ሁሉም ዜጋ ደስተኛ የሚሆንባት ሀገር እንድትሆን በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርተን እንሰራለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል፡፡
ብልጽግናዎች እውነትና እውቀትን በመያዝ ምኞትና ስሜትን መቀነስ ይጠበቅብናል ያሉት ዶክተር ዐብይ ምኞት በጥረትና ስኬት የሚከወን ካልሆነ ባዶ ተስፋ እንደሚሆንና፤ ባዶ ምኞትና ያልተገራ ስሜትም በኢትዮጵያ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሀገር ለመምራት ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት፣ ራዕይና ብቃት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ያልገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም ነገ በኢትዮጵያ ብልጽግና ላይ በጋራ ቆመን ወደኋላ ስንመለከት ይህ ውሳኔ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ታላቋን ሀገር ወደሚገባት ቦታ የሚያደርሳት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀውና የሚያየው እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልጽግና ምእራፍ እንድትሸጋገር እቅዱን በግልፅ ቋንቋ በርካቶችን በማወያየት ያዘጋጀ ሲሆን አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ ራሱን ከምኞትና ከስሜት በማራቅ አስቻይ ሁኔታዎችን አካቶ የሚመጣ ካለ ለመማር ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የየፓርቲዎቹ ሊቃና መናብርት፣ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ስምምነቱንም ዶክተር ዓቢይ አህመድ ከኦዴፓ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ከአዴፓ፣ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ከደኢህዴን፣ አቶ አህመድ ሽዴ ከሶዴፓ፣ አቶ ኡመድ ኡጁሉ ከጋህዴን፣ አቶ ኦርዲን በድሪ ከሀብሊ፣ አቶ ሀድጎ አምሳያ ከቤጉህዴፓ እና ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ከአብዴፓ ፈርመውታል።