በስፖርት ሜዳዎች የዘረኝነት ጥቃት እየተባባሰ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ
የዘረኝት ጥቃቶች፣ ዘለፋዎችና መዘዛቸው ዛሬ ዛሬ በመላው ዓለም በስፖርቱ ላይ ተጽእኖአቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በተለይ በአለማችን እጅግ ተወዳጅ የሆነው እግርኳስ፣ በተለያዩ ሊጎች ከጥቁር ተጫዋቾች መበራከት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት ጋር ተያይዞ ዘረኝነትም በዚያው ልክ እያየለ መጥቷል፡፡
የተወዳጁ ስፖርት አስቀያሚ ገጽታ-ዘረኝነት-በ2018/19 የውድድር ዓመት ብቻ በእንግሊዝ 47 በመቶ ከፍ ማለቱን የዩኬ ንግስት የህግ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዲፓርትመንት ‘ሆም ኦፊስ’ ይፋ ያደረገው ጥናት ያሳያል፡፡
ባለፈው ዓመት በተካሄዱ ጨዋታዎች ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ የጥላቻ ወንጀሎች ሪፖርት ቁጥር ከ131 ወደ 193 ከፍ ብሏል፡፡
በርግጥ ሀገራት በማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እየተናጡ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የእግርኳስ ዘረኝነት እየጨመረ መምጣት ብዙም የሚደንቅ ክስተት ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ የኢንግሊዝን የብሬግዚት ጉዳይ እና በየጊዜው እየተቀየረ የመጣውን የአሜሪካ ፖለቲካ እንኳን ለአብነት ብንመለከት ዘርና ብሔርን የተመለከቱ ክርክሮች ማዕከላቸው እየሆነ መምጣቱ ተጽእኖው አድማሱን እያሰፋ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡
በርግጥ ከዘረኝነቱ ጋር ተያይዞ የእግርኳስ ሜዳዎች ገጽታም ከወትሮው እየተቀየረ መጥቷል፡፡ በየጨዋታዎች የሚመደቡ ፖሊሶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጥናቱ ያሳያል፡፡ በአንዳንድ ጨዋታዎች ለ50 ደጋፊ አንድ ፖሊስ እስከመመደብም ተደርሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቴኮኖሎጂ ውጤቶችን በስታዲየሞች ላይ መጠቀምም ተጀምሯል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ የዘረኝነት ጥቃቶችን በማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾች መልቀቅም እየተለመደ እንደመጣ ነው የ ‘ሆም ኦፊስ’ ጥናት የሚያመለክተው፡፡ ለዚህም ውጤት የራቀው የማንቺስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች ፓውል ፖግባ እና ማርከስ ራሽፎርድ በቅርቡ ክለቡ አጣብቂኝ ውስጥ ባለበት ወቅት ያገኛቸውን የፍጹም ቅጣት ምቶች በማምከናቸው ከራሱ ከክለቡ ደጋፊዎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰነዘረባቸው ዘር ተኮር ዘለፋ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በስታዲየሞች ደጋፊዎች በብዛት የሚያሰሟቸው የዘረኝነት ዘለፋዎች እና ጥቃቶች፣ ጨዋታዎች እስኪቋረጡ ያስገደዱባቸው ጊዜያት እና ስፍራዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ያለፉትን ለታሪክ ትተናቸው በ18ኛ ሳምንት የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የታህሳስ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የቶተንሃም እና የቼልሲን ጨዋታ ክስተት እንመልከት፡፡
በቶተንሃም እና ቼልሲ ጨዋታ ምን ተፈጠረ?
ቶተንሃም በገዛ ሜዳው 2 ለ 0 በተሸነፈበት በዚህ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ከቼልሲው ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር ጋር በተያያዘ ሰን ሄዉንግ ሚን በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጣ፡፡ የቶተንሃሙ አጥቂ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው በምስል በታገዘ ዳኝነት-ቫር ጭምር በሁለቱ ተጫዋቾች በካከል በነበረ ግጭት የጫማውን መርገጫ ማንሳቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡
ይሄን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ ሩዲገር የቶተንሃም ደጋፊዎች ሰለባ ሆነ፡፡ በቆዳው ቀለም መጥቆር ብቻ ደጋፊዎቹ የዝንጀሮ ድምጽ እያሰሙ እረፍት ነሱት፡፡ ድርጊቱን የክለቡ አንበል ሴዛር አዝብሊኬታ ለዳኛው አሳወቁ፡፡ ደጋፊዎቹም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሦስት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፤ ምንም እንኳን መልሳቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ቢሆንም፡፡ይባስ ብለው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲወረውሩ ጨዋታው ለተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡
ምን እርምጃ ተወሰደ?
ጨዋታው ካበቃ በኋላ ድርጊቱ በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ ሆነ፡፡ የሀገሪቱ እግርኳስ ማህበር፣ ፐሪሚየር ሊጉና ስፖርቱ የሚመለከታቸው ሁሉ ማጣራት መደረግ እንዳለበት እና ድርጊቱን የፈጸሙ እንደሚቀጡ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አስሰሙ፡፡ ቶተንሀም ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ እና ውጤቱን ተከትሎ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ ቢያሳውቅም እስካሁን አሳማኝ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ ብዙም ባልተለመደ መልኩ በጉዳዩ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስትም ጣልቃ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ በጨዋታዎች ላይ የሚከሰተውን እጅግ አስጸያፊ የዘረኝነት ድርጊት ለመከላከል የስፖርቱ ባለስልጣናት አቅም ካነሳቸው መንግስት ጣልቃ በመግባት እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀበይ ተናግረዋል፡፡
ምንም አይነት የዘረኝነት ድርጊት በእግርኳስ ስፍራ የለውም ያሉት ቃል አቀባዩ ይሄን አስጸያፊ ድርጊት የግድ ልንዋጋው ይገባል ሲሉ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ቁርጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከፕሮፌሽናል የእግርኳስ ተጫዋቾች ማህበር እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር መንግስት በቅርበት እንደሚሰራ፣ አለፍ ሲልም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድም ነው ቃል አቀናዩ ለጋዜጠኞች የተናገሩት፡፡
የጥቃቱ ሰለባ ሩዲገርም ችግሩ አስቸኳይ እልባት እንደሚያሻው በመግለጽ ዝም ከተባለ ግን እንደወትሮው ተድበስብሶ ያልፍና እየተባባሰ ይሄዳል ሲል በትዊተር ገጹ ደጋግሞ ጠቅሷል፡፡ "የተሰነዘረብኝ የዘረኝነት ይቃት ቶተንሀምን እንደ ክለብ የሚወክል አይደለም፤ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎችም አበረታች መልእክቶችን አድርሰውኛል፤ ለዚህም አመሰግናለሁ፡፡" ሲልም ሩዲገር በጽሁፉ አስነብቧል፡፡
የቶተንሃም አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ጨምሮ በርካታ አሰልጣኞች ድርጊቱን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡
ሞሪንሆ በሰጡት አስተያየት የእግርኳስ ዘረኝነት የማህበረሰቡ ሰፊ ችግር ነጸብራቅ ነው ብለዋል፡፡ "ዘረኝነትን አምርሬ እቃወማለሁ፡፡ የዘረኝነት ጥቃት ሲፈጸም በጣም ነው የማዝነው፡፡ ዘረኝነትን ለመከላከል የሚወሰድ ማንኛውንም እርምጃ እደግፋለሁ፡፡" ሲሉም አሰልጣኙ አክለዋል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ የዘረኝነት ጥቃቶች በየጨዋታው ይሰነዘራሉ፡፡ በቅርቡ አንድ የ41 ዓመት ግለሰብ የማንቺስተር ዩናይትዱን አማካይ ፍሬድን እና አጥቂውን ሊንጋርድን በመዝለፍ ለእስራት ተዳርጓል፡፡ በተማሳሳይ ሳመንት የ13 ዓመት ታዳጊ የበርንሌይ ደጋፊ በቶተንሀሙ ደቡብ ኮሪያዊ ሰን ሄዉንግ ሚን ላይ ያነጣጠረ የዘረኝነት ምልክት በማሳየቱ ከስታዲየም ተባሯል፡፡
በሌሎች ሊጎችና የአውሮፓ ጨዋታዎችም ዘረኝነት እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ዘረኝነት ከተንሰራፋባቸው ስፍራዎች አንዷ በሆነችው ጣሊያን በአንድ የጸረ-ዘረኝነት ቅስቀሳ መርሀግብር ላይ የዝንጀሮ ምስሎችን ይዞ በመውጣት ዘረኝነትን ለመቃወም የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዷል፡፡
የተወዳጁ ስፖርት አስቀያሚ ገጽታ መባባሱ ቀርቶ፣ እልባት የሚያገኝበት ጊዜ ብዙዎች የሚናፍቁት ሆኗል፡፡