ሳዑዲ በጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ የተከሰሱ 5 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ አዘዘች
በሳኡዲ አረቢያ የሚገኘው የሪያድ የወንጀለኛ ፍርድቤት በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ከተከሰሱት ሰዎች መካከል 5ቱ በሞት እንዲቀጡ ዛሬ ታህሳስ 13 ቀን 2912 ዓ.ም. ወስኗል፡፡
የሳዑዲ አቃቤህግ ቃልአቀባይ ሻላን አል-ሻላን የካሾጊን ግድያ ምርመራ ውጤት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የመጀመሪያ ደረጃ ዉሳኔው በ11 ተከሳሾች ላይ የተላላፈ ሲሆን፣ ውሳኔው 9 ችሎቶች ከተካሄዱ በኋላ በ10ኛው ችሎት ተላልፏል፡፡
ቃልአቀባዩ ሁሉም ከካሾጊ ግድያ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩት ሲመረመሩ እንደነበረና፣ የምርመራ ውጤቱ ካሾጊን በእቅድ የመግደል ሀሳብ አለመኖሩን የሚሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ቃልአቀባዩ ከሆነ ሳኡድ አል-ቃህታኒ ከካሾጊ ግድያ ጋር በተያያዘ ምርመራ ቢደረግበትም ክስ አልተመሰረተበትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው የሳዑዲ ምክትል የደህንነት ኃላፊ አህመድ አሲሪ ከምርመራ በኋላ ክስ ስላልተመሰረተባቸው ተለቀዋል፡፡
ከተከሳሾቹ ሶስቱ ወንጀሉን በመደበቅ እስከ 24 አመት እስራት የሚያስቀጣ ዉሳኔ እንደተላለፈባቸውም ቃልአቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ምርመራ ሲደረግባቸው የነበሩት በቱርክ የሳኡዲው ዲፒሎማት ሙሀመድ አል-ቀታይቢ ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት ሌላ ቦታ መሆናቸውን በማረጋገጣቸው እንዲለቀቁ ተወስኗል፡፡