ሳዑዲ ወጣቶችን በሞት መቅጣቷን ልታቆም ነው
ውሳኔዎቹ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆኑና ይቀራል የተባለው ግርፋት ሙሉ በሙሉ ስለመሆኑም የታወቀ ነገር የለም
የአደባባይ ግርፋት ይቀራልም ተብሏል
ሳዑዲ ወጣቶችን በሞት መቅጣቷን ልታቆም ነው
ሳዑዲ አረቢያ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሰዎችን በሞት ፍርድ መቅጣቷን ልታቆም ስለመሆኑ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ውሳኔው የአደባባይ ግርፋት መቅረቱ በንጉሳውያን ቤተሰቡ ከተነገረ ከሁለት ቀናት በኋላ የተሰማ አዲስ ብስራት ነው፡፡
ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ሳይደርሱ በፈጸሙት ጥፋት ምክንያት ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩ ሁሉ ከ10 ዓመታት በማይበልጥ የእስራት ጊዜ ይቀጣሉ ተብሏል፡፡
ሆኖም ውሳኔው ከመቼ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የተገለጸ ነገር የለም፡፡ የአደባባይ ግርፋት ሙሉ በሙሉ ስለመቅረቱም በግልጽ አልተነገረም፡፡
(ፎቶ፡አሊ አል-ኒምር መንግስትን በመቃወሙ ሞት የተፈረደበት ወጣት)
እንደ ሲ.ኤን.ኤን ዘገባ ከሆነ የውሳኔው የእንግሊዘኛ ቅጂ ግርፋት ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ መወሰኑን ያትታል፡፡ የአረብኛ ቅጂው ግን ይህን አይልም፡፡ ይልቁንም የማስቀረቱ ውሳኔ የዳኞች እንደሆነ እና በሼሪዓ የተቀመጡ የቅጣት ውሳኔዎችን እንደማይመለከትም ይጠቅሳል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የተሰጠ ይፋዊ ማብራሪያም የለም፡፡
ሆኖም ንጉስ ሳልማን እና ልዑል አልጋ ወራሹ መሃመድ ቢን ሳልማን ይህን ውሳኔ የወሰኑበት ቀን ለሳዑዲ እጅግ ጠቃሚው ቀን እንደሆነ የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት አዋድ አላዋድ ተናግረዋል፡፡
በሳዑዲ የተወሰደው እርምጃ መልካም ቢሆንም የሞት ቅጣቱ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሊወገድ እንደሚገባ ተደጋግሞ መጠየቁ ግን አልቀረም፡፡ ለሰብዓዊነት እንቆማለን የሚሉ አምነስቲን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህንኑ ደጋግመው አሳስበዋል፡፡
(ፎቶ፡በጅዳ አደባባዮች 50 ጊዜ የተገረፈውና አሁንም በእስር ላይ የሚገኘው ጦማሪ ራዒፍ በዳዊ)
“የሚፈጸም ከሆነ ውሳኔው ትልቅ ብስራት ነው” ያሉት የአምነስቲ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ዋና ዳይሬክተር ሄባ ሞራዬፍ ባለፈው አመት ብቻ ሳዑዲ 184 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን ገልጸዋል፡፡
የጭካኔ የመጨረሻው ጥግ ነው ያሉትን ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ሳዑዲ በቅድሚያ በይፋ ልታግደው ከዚያም በዘላቂነት ልታስወግደው እንደሚገባም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስታወቁት፡፡