ኮሮና ቫይረስ በስፖርቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሲቀጥል የማንችስተር ሲቲና የአርሰናል ጨዋታ ተራዝሟል
ኮሮና ቫይረስ በስፖርቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሲቀጥል የማንችስተር ሲቲና የአርሰናል ጨዋታ ተራዝሟል
ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ከአርሰናል ጋር ሊያደርግ የነበረው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት አርሰናል ከኦለምፒያኮስ ጋር ባደረገው ጨዋታ በስፍራው የነበሩት የኦለምፒያኮስ ባለቤት፣ የ52 ዓመቱ ማሪናኪስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ትናንት በመረጋገጡ ነው ውሳኔው የተላለፈው፡፡
አርሰናል በጨዋታው እለት በርካታ የክለቡ ተጫዋቾች ከማሪናኪስ ጋር ንክኪ እንደነበራቸው አስታውቋል፡፡ ይሄን ተከትሎ 7 የአርሰናል ተጫዋቾች ተለይተው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡
በሌላ ዜና የእንግሊዙ ክለብ ዎልቭስ ነገ በዩሮፓ ሊግ ከኦለምፒያኮስ ጋር ይገናኛል፡፡
በግሪክ የሚካሄደው ይህ ጨዋታ እንዲራዘም ዎልቭስ ያቀረበው ጥያቄ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በማህበሩ ውሳኔ ቅሬታ የተሰማው ክለቡ አላስፈላጊ ኃላፊነት እንድንወስድ ተፈርዶብናል ሲል ተቃውሞ ቢያሰማም የማህበሩን ውሳኔ ግን እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ሁሉም የኦለምፒያኮስ ተጫዋቾች ከዎልቭስ ቅሬታ በኋላ ዛሬ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ከወደ ጣሊያን የተሰማው ዜና ደግሞ፣ የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ትናንት ባደረገው ስብሰባ ተወዳጁ የሴሪአ ዉድድር ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ላይጠናቀቅ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
የጣሊያን መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ መላው በሀገሪቱ የሚካሄዱ ውድድሮች ቢያንስ እስከ መጋቢት 25 እንደሚቋረጡ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ፌደሬሽኑ ባወጣው መግለጫ ሴሪአው የማይጠናቀቅ ከሆነ እስከተቋረጠበት ጊዜ ያለው ውጤት የመጨረሻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አሊያም የ2019/20 ውድድር ዓመት ሻምፒዮን እንደማይር ገልጿል፡፡
የሻምፒዮንስ እና ዩሮፓ ሊግ ተወዳዳሪዎችን እንዲሁም 3 ወራጅ ክለቦችን ለመለየት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሊካሄዱ እንደሚችሉም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ በአማራጮቹ ላይ ከቀናት በኋላ በፌደራል ካውንስል ውይይት ተደርጎባቸው ውሳኔ ይተላለፋል፡፡
በጣሊያን ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ውድድር ተቋርጦ የነበረው በ2004/5 የውድድር ዓመት ነው፡፡ ለመቋረጡ ምክኒያት የነበረው ደግሞ የተወሰኑ ክለቦች ከዳኛ መረጣ ጋር በተያያዘ የገቡበት የሙስና ቅሌት መሆኑ ይታወሳል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው አሁን ውድድሩ ባለበት እንዲቋረጥ ከተወሰነ በመሪነት ደረጃ ላይ ያለው ጁቬንቲዩስ ሻምፒዮን እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን ያኔ በነበረው ቅሌት ግን በቅጣት ወደ ሴሪቢ እንዲወርድ ተደርጓል፡፡
እስካሁን በጣሊያን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 10,150 መድረሱ ሲረጋገጥ 631 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
በዓለም ዙሪያ ደግሞ ከ110 በላይ ሀገራት የተዳረሰው ኮሮና ቫይረስ ከ115,800 በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ከ4,200 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ህይወታቸውን ነጥቋል፡፡