
የተባበሩት አረብ ኤሬቶች “የትንንሽ ልቦች ዘመቻ” የተሰኘ የልብ ህክምና አገልግሎት በአዲስ አበባ እየተሰጠ ነው፡፡
ሻርጃህ ቻሪቲ ኢንተርናሽናል (SCI) የተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ከሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በኢትዮጵያ “የትንንሽ ልቦች ዘመቻ” (Small Hearts Campaign) ጀምሯል፡፡
በዚህም መሰረት ድርጅቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ልብ ማዕከል ነጻ የህጻናት የልብ ህክምና በመስጠት ላይ ነው፡፡
በህጻናት ህክምና ካርዲኦሎጂስት አማካሪው ዶ/ር አህመድ አል-ካማሊ የሚመራው የህክምና ዘመቻው ቡድን፣ ሶስት ዶክተሮችን ያካተተ ነው፡፡
30 ታካሚዎችን በመለየት ባለፈው ረቡዕ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም የተጀመረው ህክምናው ለአራት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡ እስከ ነገ በሚሰጠው በዚህ የህክምና አገልግሎት በርካታ ህጻናት እንደሚታከሙም ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኤኢ አባሳደር ሞሀመድ አልራሼዲ፣ ዘመቸው ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የምታደርገው ድጋፍ አካል እንደሆነ ተናግረዋለረ፡፡
የአሁን የህክምና ቡድን አባላት ጉብኝት በልብ ህመም የሚሰቃዩ ህጻናትን ከመርዳት ባለፈ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ልምድ የሚያገኙበትም እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ዩኤኢ ባለሙያዎችን በተከታታይ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልብ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር እና የልብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሄለን በፈቃዱ ለህክምና ቡድኑ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከ 7,000 በላይ ህጻናት በማዕከሉ የህክምና ወረፋ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ሄለን፣ ማዕከሉ በቀጣይነት ከዩኤኢ ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር የቁሳቁስ እና የባለሙያ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡